Kitaaba barreessa Tasifayee G/abi irra

የቅዳሜ ማስታወሻ ተስፋዬ ገብረአብ 

አባቶችና ልጆች 

ወደ ጎንደር የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ለማስተማር የመጣ አንድ ጀርመናዊ ሃኪም አንዲት የገበሬ ሚስት እያከመ ነበር። እንዴት ሾልኮ እንደገባ ባይታወቅም የሴትየዋ ባል ከሚስቱ ራስጌ ላይ ቆሟል። ገበሬው የታመመች ሚስቱን በስስት አይን፣ ፈረንጁን ሃኪም ደግሞ በተስፋ ይመለከታል። ጀርመናዊው ሃኪም ቆጣ ብሎ ከሚስቱ ራስጌ ተጠግቶ የቆመውን ገበሬ እንዲያስወጡት አዘዘ። ረዳቶቹ ገበሬውን እየገፈታተሩ አስወጡት። ፈረንጁም ህክምናውን ጀመረ…
* * *

በግምት ከሶስት ሰአታት በሁዋላ የሰላ ጎራዴ የያዘ አንድ ገበሬ የጎንደር ሆስፒታልን ቀውጢ አደረገው። የሆስፒታሉ ሪሴፕሽን ላይ ጎራዴውን እያወናጨፈ፣ እንደ ጥይት በሚተኮስ ድምፅ ይጮህ ጀመር፣

“አምጡልኝ፣ ያንን ነጫጭባ ጣልያን! እንደ ገበሎ ወገቡን ሁለት ቦታ ላይ ካልቀነጠስኩት እኔ የአባቴ ልጅ አይደለሁም!”

ሆስፒታሉ በዚያው ቅፅበት ተተራመሰ!

ሁኔታው ወዴት እንደሚያመራ የገባቸው ነባር ሃኪሞችና ነርሶች ጀርመናዊውን ሃኪም ቢሮ ውስጥ ቆልፈውበት በውጭና በውስጥ ፈረንጁን ከበውት ለጥበቃ ቆሙ። አንዲት ነርስ ወደ ጎንደር ፖሊስ በመደወል አስቸኳይ የእርዳታ ጥሪ አደረገች። የሆስፒታሉ የጥበቃ ዘቦች አእምሮውን የሳተ የሚመስለውን ባለጎራዴ በርቀት ከብበው ይማፀኑት ጀመር፣

“እባክህ ረጋ በል!”

ገበሬው ግን ሊረጋጋ አልቻለም።

“ገለል በሉ ከፊቴ! ሁዋላ ሰበብ ትሆናላችሁ! ከእናንተ ጠብ የለኝም! ገለል በሉ ብያለሁ…”

“እባክህ ረጋ በል ጌታው! ጎራዴውን አስቀምጥና እንነጋገር!?”

“በህግ አምላክ ሰበብ አትሁኑብኝ!”

ገበሬው ጎራዴውን ልክ እንደ ገብስ አጨዳ አይነት፣ አየሩ ላይ እየሰነዘረ፣ አየሩን በሰላ ጎራዴው ያጭደዋል። እንደሚገነፍል የጀበና ቡና ያለ የእልህ ቁጣ ከልቡ ብልቃጥ እየተተኮሰ፣ እንደ ማቅራራት ያደርገዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጀርመናዊው ሃኪም እጅና እግሩ እየተንቀጠቀጠ ወደ ጀርመን ኤምባሲ ለመደወል ቢጠይቅም፣ እጁን ይዘው እንደምንም አረጋጉት። ባለ ጎራዴው ገበሬ ዘቦቹን ጥሶ ቢመጣ እንኳ፣ የሆስፒታሉን ሃኪሞችና ነርሶች ገድሎ ሳይጨርስ እሱ ዘንድ ሊደርስ እንደማይችል በእርግጠኛነት ቃላቸውን ሰጡት።

በዚህ መካከል ፖሊሶች ደረሱ። እነርሱም እንደ ዘቦቹ፣ ጠመንጃቸውን አቀባብለው ገበሬው ላይ በመደገን ጎራዴውን እንዲያስቀምጥ መማፀን ጀመሩ። ግማሽ ሰአት እንኳ ባልወሰደው በዚህ ቅፅበታዊ ግርግር ውስጥ፣ በሆስፒታሉ ውስጥ ነባር የሆነ አንድ የአስተዳደር ሰራተኛ መፍትሄ አበጀ። በሆስፒታሉ ውስጥ ለህክምና ከተኙ ከበድ ያሉ አዛውንቶች መካከል ሁለቱን መርጦ በማምጣት፣ ወደ ባለጎራዴው ተጠግተው እንዲያነጋግሩት ፖለሶቹም ገለል እንዲሉ አደረገ።

ከአስር ደቂቃ በሁዋላ ባለጎራዴው ረገብ አለ። ጎራዴውን ማወዛወዙንም ቀነሰ። በመቀጠል ስለተፈጠረው ችግር ለጀርመናዊው ሃኪም ገለፃ ተደረገለት። ገበሬው ለምን ሊገድለው እንደመጣ ለጀርመናዊው ማብራሪያ ሲደረግለት፣ በድንጋጤ ደሙ ከፊቱ ላይ ጥርግርግ ብሎ ጠፍቶ፣ ያልተፃፈበት ነጭ ወረቀት መስሎ እንደነበር አጠገቡ የነበሩት መስክረዋል። ሆኖም ችግሩ ሊወገድ እንደሚችል በእርግጠኛነት ነገሩት። በርግጥ ገበሬውን በቁጥጥር ስር ማድረግ እንደሚቻል ነግረውታል። መፍትሄ እንደማይሆን ግን አስረዱት። የገበሬው ዘመዶች ሊበቀሉት እንደሚችሉ በመጠቆም፣ የሚሻለው እርቅ መሆኑን ጠቆሙት።  ጀርመናዊው ሃኪም ምን ጥፋት እንደፈፀመ በትክክል ሊገባው ባይችልም የተፈጠረውን ከፍተኛ ግርገር በመመልከት አንድ አደገኛ ነገር መከሰቱን ተገንዝቦ ስለነበር፣ ምንም ሳያመነታ ገበሬውን ይቅርታ ለመጠየቅ ተስማማ፣

* * *

እነሆ! ገበሬውና ሃኪሙ በሰዎች እንደታጀቡ በየተራ የገበሬው ሚስት ወደተኛችበት የበሽተኛ ክፍል እንዲገቡ ተደረገ። ገበሬው ጎራዴውን እንደጨበጠ ከሚስቱ ራስጌ አጠገብ ቆመ። ጀርመናዊው ሃኪም ከበሽተኛዋ አልጋ ግርጌ በኩል እንዲቆም አደረጉት። አሸማጋዮቹና የሆስፒታሉ ጥቂት ዶክተሮች በመካከል ላይ ቆሙ። በአገሩ ባህል መሰረትም አሸማጋዮቹ የተፈጠረውን ችግር በዝርዝር አብራሩ። ከዚያም በአስተርጓሚ በኩል ፈረንጁን እንዲህ አሉት፣

“የህመምተኛዋን የተከበሩ ባል በማመናጨቅ መልኩ እጅህን አወዛውዘህ፣ ‘አስወጡት!’ ማለትህ ልክ አይደለም። እሳቸው ባለቤታቸው እንደመሆናቸው ከዚህ መውጣት ካለባቸውም በጨዋ ደንብ ለብቻቸው ገለል በማድረግ ሊነገራቸው ይገባል እንጂ፣ ሚስታቸው ፊት በዚህ መንገድ ማመናጨቁ ክብር የሚነካ ነው። እሳቸውም እንዲህ ሚስታቸው ፊት ክብራቸው ተነክቶ፣ አባወራ ሆነው መኖር ስለማይችሉ ጎራዴያቸውን ይዘው መጥተዋል። ርግጥ ነው፣ እርስዎም እንግዳችን እንደመሆንዎ መከበር አለቦት። እንዲህ ያለ ነገር በመፈጠሩም አዝነናል። የእግዚአብሄር ፀጋ አልተለየንምና ግን በመካከላችሁ ደም አልፈሰሰም። አሁን እርስዎም በደል እንደፈፀሙባቸው አውቀው፣ በሚስታቸው ፊት ይቅርታ ይጠይቋቸው!”

ጀርመናዊው ሃኪም በሽማግሌዎቹ በተመከረው መሰረት በአስተርጓሚ ምላሽ ሰጠ፣

“በእውነቱ እሳቸው የህመምተኛዋ ባል መሆናቸውን አላወቅሁም ነበር። የአነጋገር ጠባይና ልማድ ሆኖብኝ እንጂ ማመናጨቄም አልነበረም። ከሃገሬ ድረስ ሌሊትና ቀን ተጉዤ እዚህ መምጣቴ የታመሙትን ለመርዳት እንጂ ክብር ለመንካት አይደለም። መቼም አጥፍቼ ከሆነ እሳቸውንም ባለቤታቸውንም ይቅርታ እጠይቃለሁ!”

ሃኪሙ የተናገረው ለገበሬውና ለሚስቱ ተተርጉሞ ሲነገራቸው፣ ሁለቱም ስሜታዊ ሆነው በነጠላቸው ጫፍ አይኖቻቸውን አባብሰዋል። ገበሬውም በዚያችው ቅፅበት ጎራዴውን ከሽማግሎቹ ለአንዱ ካስረከበ በሁዋላ፣ የሚከተለውን ተናገረ፣

“እኔም ብሆን ሚስቴን ከህመሟ ይፈውሱልኛል ብዬ ተስፋ ያደረግሁት በርስዎ ላይ ነው። የክብር ነገር ሆነብኝና ግን አስቀየምሁዎ! ጣሊያን መስለውኝ ያለ ስምዎ ስም በመስጠቴና በመዝለፌ እኔም ብሆን ይቅርታ እጠይቃለሁ። ሊያጠቃኝ ጎራዴ መዘዘብኝ ብለው በልብዎ ቂም ይዘው ሚስቴን ችላ እንዳይሉብኝም ርስዎም ቃሎን ይስጡኝ”

ይህ የገበሬው ንግግር ለፈረንጁ ሃኪም ሲተረጎምለት ፊቱ የማረቆ ድልህ መምሰሉ ታይቶአል። ሚስትየዋ አንዳችም ያልተናገረች ሲሆን፣ ፈረንጁ ይቅርታ ሲጠይቅ ግን ከወገቧ እንደመነሳት ብላ፣ “አይገባም” እንደማለት አክብሮቷን ገልፃለታለች። በዚህ መልኩ እርቁ ከተፈፀመ በሁዋላ ሁለቱ በእድሜ የሚቀራረቡ ባላንጣዎች ትከሻ ለትከሻ እንዲሳሳሙ አደረጓቸው።

* * *

ይህን ታሪክ ያጫወተኝ በወቅቱ ከኮሌጁ የህክምና ተማሪዎች አንዱ የነበረ ጓደኛዬ ሲሆን፣ ታሪኩ ከተፈፀመም 19 አመታት ሆኖታል። ሆኖም ይህ ታሪክ አእምሮዬ ላይ ነግሶ እንደመኖሩ፣ የክብር ጉዳይ በተነሳ ቁጥር በጨዋታ መሃል ስጠቅሰው ኖሬያለሁ። ርግጥ ነው፣ ያ የበጌምድር ገበሬ ከኛ ዘመን ትውልድ ጋር የመንፈስ ዝምድና ይኖረዋል ለማለት ቃጥቶኝ አያውቅም። የ18ኛው ክፍለዘመን አበሾች ወደመቃብራቸው ሲጓዙ፣ “እኛ እንዲህ ነበርን” ለማለት ለምልክት ትተውት የሄዱት መስሎ ይሰማኛል።      

 

የውሾች መብት ጉዳይ! 

“እኛና የእኛ ከብቶች” በሚል ርእስ የፃፍኩትን መጣጥፍ አስመልክቶ በርከት ያሉ ደብዳቤዎች ደርሰውኛል። አንዳንዶቹ ሲጨመቁ እንዲህ የሚሉ ነበሩ፣

 “ለፓርላማ ሊቀርብ የተዘጋጀው ህግ የከብቶችን ብቻ ሳይሆን፣ የውሾችንና የሌሎች እንስሳትንም መብትና አያያዝ የሚመለከት ነው። አንተ ግን ‘የእንስሶች መብት’ ከሚለው ውስጥ የከብቶችን ብቻ ነጥለህ በማውጣት አጣመህ አቀረብከው። የመቃወም በሽታ የለከፈህ ይመስላል” የሚል ነበር። ከተሳሳትኩ መቼም ይቅርታ! ግን ስለ ውሾችም ቢሆን መነጋገር ይቻላል!…. 
ርግጥ ነው፣ እንደ አበሻ ውሻ በአለም ላይ ፍዳና መከራ የሚያይ ውሻ አለ ለማለት አይቻልም። ችግሩ ይገባኛል። ውሾችን፣ ድመቶችን፣ ወፎችን በድንጋይና በወንጭፍ ማሳደድ ከልጅነት ጨዋታዎቻችን ዋነኞቹ ነበሩ። ግን እኮ ሌላ መጫወቻ አልነበረንም። አሁንም ቢሆን የለም። በጥቅሉ ግን ውሾቻችን መራባቸውና መደብደባቸው ሳይበቃ፣ ስድብ ቀለባቸው ነው። ልክስክስ፣ ጭራውን የሚቆላ፣ ውሻ በበላበት….ኸረ ስንቱ ተቆጥሮ ይቻላል? የአበሻ ውሻ በልቶ ቢሰደብ እንኳ ባልከፋ። ታማኝ ሆኖ ባገለገለ ስድብ ቁርሱ፣ በፍልጥ ወገቡን መመታት ራቱ መሆኑ ያሳዝነኛል። ኢህአዴግ በማርቀቅ ላይ ያለው የውሻ መብትና አያያዝ ህግ ፀድቆ፣ ውሾቻችን ነፃ ቢወጡ በጣም ደስ ይለኛል።  

ብዙ መጤን ያለባቸው ጉዳዮች ግን አሉ… 
እኔ ጋዜጠኛ ሆኜ አዲሳባ በነበርኩበት ጊዜ የአዲሳባ የግብርና ቢሮን አመታዊ ሪፖርት ተመልክቼ እንደነበር አስታውሳለሁ። በወቅቱ የክልል 14 የግብርና ቢሮ በ1988? ባቀረበው አመታዊ የስራ ሪፖርት ላይ፣ “524 የጎዳና ውሾች ገደልን” የሚል ነበረበት። ለነገሩ አዲሳባ እርሻ ሳይኖራት ግብርና ቢሮ ማቋቋሟ ገርሞኝ ነበር። ግብርና ቢሮው የተቋቋመው በስህተት ሳይሆን አልቀረም። ከሚዘጋ በሚል ግን ውሻ እንዲገድሉ አዘዟቸው። በዚህ ምክንያት ከአመት አመት፣ የአዲሳባን ባለቤት የሌላቸው ውሾች እያሳደዱ መግደል ስራቸው ሆኖ ከረመ… 
እንግዲህ አሁን “የውሾች መብት ይከበር” ከተባለ፣ የአዲሳባ ግብርና ቢሮ ምን ሊሰራ ነው? በርግጥ ቢሮው አሁን ይኑር አይኑር አላውቅም። የውሾች መብት ህግ ከፀደቀ ግን ቢሮው ለውሾች መጠለያ እና ምግብ ማዘጋጀት ሊኖርበት ነው። ፍቅሩ ኪዳኔ ባሳተመው መፅሃፍ ላይ፣ ፈረንሳይ ለድመትና ለውሻ በአመት 70 ቢሊዮን ብር እንደምታወጣ መፃፉ ትዝ ይለኛል። የኢህአዴግ ፓርላማ ይህን ህግ ከማርቀቁ በፊት ካዝናውን መፈተሽ አለበት። ለሁሉም ክልሎች ውሾች ያለ አድልዎ ተመጣጣኝ በጀት መመደብም ይጠበቅበታል። ቢያንስ መሰረታዊ ለሆኑት ምግብና መጠለያ ማለት ነው። 
ችግሩ ግን በዚህ ብቻ አያበቃም። ባለቤት ያላቸው ውሾች ጉዳይም አለ። 
የኛ ውሾች እንደሚታወቀው የመዝናኛ አይደሉም። ዘብ ናቸው። “ምግብ ለስራ” በሚል ስም ቁራሽ የብጣሪ ቂጣ እየተወረወረላቸው፣ በረሃብ ሆዳቸው ከወገባቸው ተጣብቆ፣ ሌሊቱን ሙሉ ከሌባና ከጅብ ሲተናነቁ የሚያድሩ ለጌቶቻቸው ፍፁም ታማኝ የሆኑ ፍጡራን ናቸው። የሚጠጣ ውሃ በማጣት የሚያብዱ ውሾች ቁጥር የላቸውም። በጅብ እየተነከሱ በቁስል የሚሰቃዩ ውሾች ህክምና አያገኙም። “የውሾች አያያዝ” ሲባል መንግስት በመላ ሃገሪቱ ለውሾች የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ክሊኒክ ሊከፍት ተዘጋጅቶአል? ይሄ ቀርቶ ውሾች በቀን አንድ ጊዜ እንዲመገቡና ውሃ እንዲጠጡ ለማድረግ እንዴት ይችላል? 
የውሻ አስተዳደግ ሌላው አከራካሪ አጀንዳ ሊሆን ነው።  
የአበሻ ውሻ ክፉ እንዲሆን፣ እንደ ቃሊቲ ልዩ የእስር ክፍል ጨለማና ጉድጓድ ውስጥ ተቀብሮ ነው የሚያድግ። ይሄ እጅግ አሰቃቂ የሆነው የውሻ አስተዳደግ በህግ ከታገደ ውሾች ሃይለኛ እና ክፉ ሊሆኑ አይችሉም። ሌሊት ሌባ ሲመጣም እንደ ድመት እግሩን እየላሱ፣ “እንኳን ደህና መጣህ፣ ግባ!” ሊሉት ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ የውሾች መብት ህጉን ከማፅደቁ በፊት፣ በየቀበሌው ጅብና ሌባ የሚጠብቁ ፖሊሶችን ማሰማራት አለበት። ምክንያቱም የበርካታ መንደሮች እንስሳት፣ ጎተራዎችና ንብረት እየተጠበቁ ያሉት በእነዚህ ክፉ ውሾች ነው። የውሾች መብት ከተከበረ ውሾቻችን እንደ ፈረንጅ ውሻ ለስላሳ ሊሆኑብን ነው። ለዚህ ክፍተት ማሟያ ምን ተዘጋጅቶአል? 
ረቂቅ ህጉን ያዩ እንደሚናገሩት፣ “ውሻን መደብደብ በህግ ያስጠይቃል” የሚል አንቀፅ አለበት። በርግጥ ውሾቻችን እንደሚደበደቡ መካድ አይቻልም። ሆኖም ውሾች በፍልጥ ወገባቸውን የሚመቱበትን ምክንያት ማወቅ ይገባል። ብዙውን ጊዜ ውሾች ስለሚርባቸው፣ ማድቤት አካባቢ አይጠፉም። አዘናግተው በመጠበቅም፣ ቡሃቃ ይለክፋሉ። ሙልሙል ይሰርቃሉ። መሶብ ይገለብጣሉ። በዚህ ጊዜ በፍልጥም ሆነ በተገኘው ነገር ሁሉ ወገባቸውን ይመታሉ። በስርቆት ሰበብ ወገባቸው ተመቶ ሽባ የሚሆኑና በዚያው የሚሞቱ ውሾች በጣም ብዙ ናቸው። በዚህ የኑሮ ውድነት ለውሾች በቂ ምግብ ማቅረብ አይቻልም። ውሾች ከተራቡ ደግሞ ለመስረቅ ይገደዳሉ። ከሰረቁ ይደበደባሉ። ይሄን ችግር እንዴት መፍታት ይቻላል? ውሾቹ ወደ ፖሊስ ሊከሰሱ ወይስ የምክር አገልግሎት ሊሰጣቸው? በምን ቋንቋ? በዚህ ዘመን እንኳን ሰውና ውሻ፣ ሰውና ሰው እንኳ በቋንቋ መግባባት እየተቸገረ ነው። 
ህግ ማውጣት ቀላል ነው። ህጉ በአዲሳባ ለሚኖሩ የፈረንጅ ውሾች ከሆነ፣ እነርሱ በደል ደርሶባቸው አያውቁም። መልካቸውን አሳምረው ሳሎናቸው ናቸው። ለምናውቃቸው ነባር የአበሻ ውሾች ግን ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አይመስልም። እንደ ምርጫ ህጉ የማይፈፀም ህግ ከማርቀቅ ደግሞ ቢቀር ይሻላል….           

በጎንደር ማዘጋጃ ቤት በጭካኔ የተገደለውን ውሻዬን (ፖኒ ይባላል አፈሩ ይቅለለውና) አስታወስከኝ። አፈሩ ይቅለለው ያልኩት ባግባቡ ከጓሮአችን መቃብር አብጅቼ እና የሕይወት ታሪኩን ፅፌ ግብዓተ-መሬቱን ስለፈፀምኩ ነው።ፖኒ (ድንክ ፈረስ ማለት ነው) ሌባ ሳያንዣብብ በማያድርበት መንደራችን በጣም ታዋቂ ንቁ የሌባ ጠር ነው። ምንም እንኳን ግቢያችን ለመዝለል የሚያዳግት አጥር ቢኖረውም የፖኒ የአደጋ ጊዜ ጩኸት እንኳን ሌባን ቀርቶ የተኛ ጎረቤትን ያሸብራል። (ፖኒ ዛሬ በሕይወት ቢኖር ወያኔ በአሸባሪነት ይከሰው ነበር) ታዲያ አንድ ቀን የጎንደር ማዘጋጃ ቤት (መጋጃ ቤት፡ በኛ የዚያን ጊዜ አጠራር) የተለመደ የሌሊት የጎዳና ውሻዎችን የመግደል ዘመቻ ሲያካሂዱ ያለወትሮአቸው በኛ በር በኩል ማለፍ። አጅሬ ፖኒ ማናባቱ ነው በእኩለ ሌሊት እንደ አጋንንት የሚሩዋሩዋጠው ብሎ ከግቢያችን አጥር ዳር እስከዳር እየሮጠ ማንባረቅ። ከዚያም የመጋጃ ቤት ውሻ ገዳዮች በመርዝ የተለወሰ ሥጋ ባጥር አዘልለው ወደ ግቢያችን መጣል። በጠዋት ታላቅ እህቴ ቀስቅሳ የፖኒን መሞት ስታረዳኝ እዚያው ደንዝዤ ብዙ እንደቆየሁ አስታውሳለሁ (ማጋነን ባይሆን ልክ ጆርጅ ቡሽ የሴፕቴምበር 11 ጥቃት ሲነገረው ለ15 ደቂቃ በሚጎበኛቸው ተማሪዎች ክፍል ፊት ለፊት ደርቆ እንደቀረው ማለት ነው)። የፖኒ መገደል ለኔ ትልቅ ሽብር ነበር። ፖኒ ታናሽ ወንድሜ ነበር። የቤታችን በር የድንጋይ ንጣፉ ላይ በጎኑ ለጥ ብሎ ሲታይ የዘላለም ሳይሆን ጊዜያዊ እረፍት የሚያደርግ ነበር የሚመስለው – ፖኒ። ሁሌም ያ ምስል ከአዕምሮዬ አይጠፋም። ገዳዮቹንም ይቅር አላልኩዋቸውም። 

ክብሩ ውሻህ በእንዲህ ዓይነት መሞቱ በጣም አሳዝኖኛል፡፡ እኔም አንዳንድ ያልገባቸው የማዘጋጃ ቤት ሰራተኞች ያበደ ዉሻ ወይም ባለቤት የሌላቸው ዉሻ ግደሉ ሲባሉ እነሱ ደግሞ በተገላቢጦሽ ባለቤት ያለውና የሌለው እየገደሉ እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡ የኛ ጎረቤት እንደ ሃብታም ተንከባክበው ያሳደጉት ዉሻቸው በእንዲህ ዓይነቱ መግደላቸውን አስታውሳለሁ፡፡ 

እነዚህን የእንስሳት ተረቶች ሳነብ ሌላ ሁለት ተረቶች በሀሳቤ መጡ፡፡ አንደኛው በጽድቅና ኩናኔ ላይ የተቀለደ ነው፡፡ ስብከት የበዛበት ምእመን ይህ የምትሉኝን ነገር አይቶ መጣ አለ ወይስ ጭምጭምታ ነው ብሎ የጠየቀበት፡፡ ሌላው ደግሞ በግምት አዲስ አበባ ደጋ ነው ያለውን የኛ አካባቢ ሰው አዲስ አበባን ታውቀዋለህ እንዴ ብለው ሲመይቁት አላውቀውም፡፡ ይልና ታዲያ እንዴት ደጋ መሆኑን አወቅክ ሲባል ብርድ ልብሱ የሚመጣው ከዚያ ስለሆነ ያለውን ለማለት ነው፡፡ መቼም ለተስፍሽ የጽሁፍ ችሎታ ማረጋገጫዎች አንዱ እዚህ ግባ የሚባል ሀሳብ ሳይኖራቸውም ጭምር የሚነበቡ ጽሁፎቹ ናቸው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ከሆነ የሁለቱም ጽሁፎች ጭብጥ ወይ ግምት ወይ ጭምጭምታ ብቻ ነው፡፡ እንስሳቱ የሚፈልጉትንና የሚመቻቸውን የሚያውቅ የለም፡፡ አንተ ምን ትገምታለህ ካላችሁኝ ግን ለአንድ ኢትዮጽያዊ እንስሳ ኢትዮጽያዊ አያያዝ ሳይሻለው የሚቀር አይመሰለኝም፡፡ 

 

የቅዳሜ ማስታወሻ ተስፋዬ ገብረአብ 

መለስ ዜናዊ! – በማን ይተካል? 
ወቅታዊውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ የሃይል አሰላለፍ በመገምገም፣ “መለስ ዜናዊ! – በማን ይተካል?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት በርግጥ ቀላል አይደለም። በቅድሚያ ግን “በርግጥ መለስ ዜናዊ ስልጣኑን ይለቃል?” ብሎ መጠየቅ ይገባል። መለስ ዜናዊ፣ “ከሁዋላ ሆኜ ማገዜ ባይቀርም፣ እለቃለሁ” ብሎ ደጋግሞ ነግሮናል። ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፣ “መለስ እለቃለሁ ቢልም ባይልም አፍንጫውን ተይዞ ይለቃል” ሲሉ ቁጣ ባዘለ ድምፅ እየገለፁ ነው። የሆነው ሆኖ በራሱ ፍላጎትም ሆነ ተገዶ መለስ ስልጣኑን መልቀቁ የማይቀር ከሆነ ቀጣዩ የኢትዮጵያ መሪ ማን ይሆናል? በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ተንትኖ የፃፈ አላጋጠመኝም…

ስዬ እና ብርቱካን…?

ሁለቱ የፖለቲካ ሰዎች (አይን ካረፈባቸው) የቀጣዩ ዘመን የኢትዮጵያ መሪዎች መካከል መሆናቸው ይወሳል። መቼም አሜሪካኖች ለኛ ካላቸው የተቃጠለ ፍቅር የተነሳ፣ የአፍሪቃ ቀንድ ችግር ያሳስባቸዋል። በፖለቲካውም በረሃቡም መሃንዲስና በጎአድራጊ ናቸው። “የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ተጣምረው አንድ ሃይል መሆን አቃታቸው እንጂ ባገዝናቸው ነበር” ሲሉ ማማረራቸው ብዙ ጊዜ ይሰማል። ያሬድ ጥበቡ የበረከትን መፅሃፍ በተቸበት መጣጥፉ፣  “የስዬና የአሜሪካኖችን መቀራረብ” በጨረፍታ አጫውቶናል። በይስሃቅ ኤፍሬምና በብርቱካን ሚደቅሳ መካከል “የቀጠለው” ግንኙነትም እንዲሁ ርእሰወግ ሆኖ ሰነባብቶአል። የስዬ አብርሃ አስፈላጊነት በአሜሪካኖቹ ከታመነበት ቆየ። ስዬ በህወሃትና በተቃዋሚዎች መካከል ድልድይ እንዲሆንላቸው ይፈልጋሉ። ሰራዊቱንም እንደነበረ ያቆይላቸዋል። ጄኔራል ሳሞራን ከላይ ነጥሎ በማንሳት ብቻ የሰራዊቱን መዋቅር እንደነበረ ለማስቀጠል፣ ስዬ ሁነኛ ምርጫቸው ነው። የከፋ ነገር ከመጣ መለስም ቢሆን በዚህ ይስማማል። ስዬን በቀጥታ በመለስ ቦታ ማስቀመጡ ግን አስቸጋሪ ነው። ብርቱካን ከላይ ብትሆን ሚዛኑ ሊጠበቅ ይችላል። ሴት መሆኗ እና የገነባችው ስም፣ የወጣችበት ማህበረሰብ ሁሉ ሚዛናዊ ያደርጋታል” ይላሉ። ማሰብ ችግር የለውም። ምን ችግር አለው?

ሃይሌና መሃመድ….?
ሃይሌ ገብረስላሴና መሃመድ አላሙዲ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ያስቡ ይሆን? ሁለቱም ከጀርባ ግፊት አለባቸው። የኛ ሰው መቼም ክፉና ተንኮለኛ ነው። ከፈገግታ ጋር ወደ ጆሮ ጠጋ ብሎ ማሳሳት ይችልበታል። 

“ሼክ መሃመድ…ህዝቡ እኮ ‘እሳቸው ቢመሩን ይሻል ነበር’ እያለ ነው። ቢያስቡበት ጥሩ ነው…”

“ሃይሊሻ! ለምን አትወዳደርም? የላይቤሪያው ጆርጅ ዊሃ እንኳ ተወዳድሮአል። ህዝቡ ግልብጥ ብሎ ነው የሚመርጥህ…”

ታምራት ላይኔ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበረ ጊዜ ይህንኑ የአላሙዲ ፍላጎት አጫውቶኝ ነበር። ቃለመጠይቅ አድርጌው ካበቃን በሁዋላ ስናወጋ፣ “የሼኩ የረጅም ጊዜ እቅዱ ወደ ፖለቲካው መግባት ነው። ከሆነለት አገሪቱን መምራት ይፈልጋል” ብሎ እንደነገረኝ አስታውሳለሁ። አሁን እንኳ አሳቡን ሳይለውጥ አልቀረም። በወርቅ ቁፋሮ ተጠምዶአል። ከእለታት አንድ ቀን የኢትዮጵያ ህዝብ ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ ትልልቅ ባዶ ጉድጓዶችን ያገኛል።  የሃይሌ ገብረስላሴን ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ጉዳይ ለመለስ በጥያቄ መልክ አቅርበውለት ነበር። 

“…ይህን በተመለከተ ከሃይሌ ጋር አላወራንም” ሲል መልስ ሰጠ። አያያዘናም የማስጠንቀቂያ ወንድማዊ ቃል አከለበት፣ “….ሃይሌ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ውጤታማ ይሆናል ወይስ አይሆንም የሚለውን ለመፍረድ አልችልም። ሆኖም ወደ ፖለቲካ የመግባት ሙሉ መብት አለው…” በውነቱ መለስ ሃይሌን ደግ መክሮታል።

ሁለቱ ታዋቂ ሰዎች ከቀጣዩ ዘመን የጠቅላይ ሚኒስትርነት የስም ዝርዝር ላይ እጃቸውንም ሆነ ስማቸውን ባያስገቡ ይጠቅማቸዋል። ይልቁን መለስን በመምከርና ታሪካዊ ምርጫ አካሂዶ፣ ታሪክ እንዲሰራ ቢያግባቡት እነርሱንም ታሪክ ሲያስታውሳቸው ይኖራል።

እነ ተወልደ…?

“እነ ተወልደ” በሚል ተውላጠ ስም ከሚታወቁት መካከል እንደገና አንሰራርቶ ወደ ስልጣን የሚመለስ ሊኖር ይችላል? አይመስለኝም። እነ ተወልደ ከፖለቲካው ርቀዋል። ለነገሩ ባመለካከትም ተለያይተዋል። ልዩነታቸው በፈረደባት ኤርትራ ዙሪያ ነው። ተወልደ ከመለስ ጋር የከረረ እልህና ፀብ ቢኖረውም፣ በአሰብና በኤርትራ ሉአላዊነት አጀንዳ ላይ አሁንም በአቋሙ ላይ እንደፀና መሆኑ ይሰማል። የስዬ፣ የገብሩና የጆቤን ቅስቀሳ፣ እንደ ደጋፊ መፈለጊያ ብቻ የያዋል። አለምሰገድ ገብረአምላክና ሰለሞን ጢሞም በተመሳሳይ በተወልደ መንገድ በመጓዝ ላይ ናቸው። ቀሪዎቹ የህወሃት አንጋፋዎች ወደ ቢዝነሱ አለም ገብተዋል። ፃድቃንና ጃማይካ፣ “ራያ” የተባለውን ቢራ ለመገንባት እንቅልፍ አጥተዋል። ፃድቃን ከደቡብ ሱዳን ያገኘውን ገንዘብ ወደ ማሌዢያ ባለማሸሸቱ ሊመሰገን ይገባዋል። ሃይለኛ እና ተሳዳቢ የነበረው ቢተው በላይ እንኳ፣ እንዲህ ረግቦ በቢዝነሱ ላይ መወሰኑ ያስደንቃል። ታስሮ ከተፈታ ወዲህ ፀጥተኛ ሆኖአል። አሁን አሁን፣ እስርቤት ገብተው የሚወጡ ፖለቲከኞች ጠባያቸው ለምን እንደሚለወጥ ሊገባኝ አልቻለም። የሚወጓቸው መርፌ ይኖር ይሆን? በጥቅሉ እነ ተወልደ ከወደፊቷ ኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ያነሱ ይመስላሉ። መልካም የጡረታ ዘመን እንመኝላቸዋለን። 

ፍሰሃ እሸቱ….?  

ፍሰሃ በግልፅ ቋንቋ፣ “ስልጣን አልፈልግም” ብሎ ተናግሮአል። አያይዞም፣ “እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ ነፃነት የሚገኝበትን አቋራጭ መንገድ ላሳያችሁ ነው የመጣሁት” ብሎናል። እንደ ፍሰሃ እቅድ በውጭ አገር የተበተኑትን እና በነገር ካራ ርስበርስ የሚወጋጉትን ተቃዋሚዎች በማስታረቅ በመጪው ሰኔ ወር ላይ አንድ ካውንስል ያቋቁማል። ከፖለቲካ ርቆ የተቀመጠውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ማንቀሳቀስ እንደሚችልም በርግጠኛነት አብራርቶአል። ያን ጊዜ፣ እንደ ፍስሃ ህልም 50 ሺህ ኢትዮጵያዊ ተቃዋሚ “እንደ ቆላ ወፍ – እንደ ግሪሳ” ዋሽንግተን ዲሲ ነጩ ቤተመንግስት ደጃፍ ላይ ይጥለቀለቃል። ይህ ሲፈፀም፣ አሜሪካና መላው አለም የኢትዮጵያን ህዝብ የነፃነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ማዳመጥ ይጀምራል። 50 ሺህ ተቃዋሚ እንደ ግሪሳ ዋሽንግተንን ሲያንቀጠቅጣት በኢትዮጵያም በተመሳሳይ አመፁ ይፈነዳል። እናም አፋኙ የመለስ ስርአት በመጪዎቹ ስድስት ወራት፣ (ከመስከረም 2012 ወዲህ) የስልጣን እድሜው ያበቃለታል። ካውንስሉም የሽግግር ሂደቱን ተረክቦ ቀጣዩን የምርጫ ስርአት ይዘረጋል። 

መቸም ፍሰሃ እሸቱ በቃል እንዲህ ቀለል አድርጎ እንደተነተነው በተግባር መፈፀም ከቻለ፣ እሱ “ስልጣን አልፈልግም” ቢልም የኢትዮጵያ ህዝብ፣ አስገድዶ የጠቅላይ ሚኒስትርነቷን ወንበር ያስረክበዋል።  እንግዲህ በቅርቡ ደግሞ “ከፍሰሃ ጀርባ እነ አጅሬዎቹ አሉ”  የሚል ሹክሹክታ ያነበብኩ ይመስለኛል። ከሆነ በርግጥ ሊሳካለት ይችል ይሆናል። የሆነው ሆኖ ፍሰሃ ራሱን ከወደፊት እጩ መሪዎች አንዱ አድርጎ ፈጥሮአል…

ብርሃኑና አንዳርጋቸው…?

ብርሃኑ ነጋ እና ግንቦት 7 የስልጣን ፍላጎት እንደሌላቸው ገና ከመነሻው ግልፅ አድርገዋል። ይህን አባባል ግን ተቀብዬው አላውቅም። በፕሮግራማቸው መሰረት ትግሉን መርተው ድል ማድረጉ ከተሳካላቸው በወደፊቱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሳይወዳደሩ ዳር ላይ ይቆማሉ ተብሎ አይታሰብም። እንደምናየው የተከተሉት የትግል አቅጣጫ ፈተና የበዛበት ሳይሆን አልቀረም። እንደ ድመት 9 ነፍስ ያላቸው ይመስል፣ የሞት ፍርድ ሜዳሊያ ተሸክመዋል። ከወያኔ እስርቤት የተከተቱ ብዙ አባላት አላቸው። በተግባርም ሆነ በፕሮፓጋንዳው ወያኔን በብርቱ እየተፈታተኑት ነው። የትጥቅ ትግል የሚከተሉ እንደመሆናቸው፣ ምን እየሰሩ እንዳሉ ማወቅ አይቻልም። ብዙውን ጊዜ ምን እየሰሩ እንዳሉ የሚነግረን ወያኔ ነው። “ሊገሉኝ ነበር – ያዝኳቸው! ሊያፈነዱ ነበር – አከሸፍኩት!” ይለናል። ከከማል – ኦነግ፣ ከአፋርና ከህብረብሄራዊ ድርጅቶች ጋር የጋራ ግብ ነድፈው በመጓዝ ላይ ናቸው። በመሆኑም ብርሃኑ እና አንዳርጋቸውም መጪዋን ኢትዮጵያ ለመረከብ አማራጭ ሆነው ይታያሉ…
አረጋዊና ግደይ…?

አረጋዊና ግደይ ህወሃትን መስርተው ሲያበቁ ከህወሃት ተባረሩ የፖለቲካ ሰዎች ናቸው። ስለሁለቱ ሰዎች ሳስብ በሚዲያ ብቻ ከሚያደርጉት አስተዋፅኦ ባሻገር፣ ለምን ወደ መሬት ወርደው እንደማይንቀሳቀሱ አላውቅም። “ደሚት” በሚል ስም የሚጠሩትን የትግራይ አማፅያን ለምን ማግኘት እንደማይፈልጉም አይገባኝም። በተጧጧፈው ትግል ውስጥ ሙሉ ተሳታፊ ሆነው አይሰሙኝም። ምርጫ ሲደርስ ብቅ ይላሉ። መልሰው ደግሞ እልም ይላሉ። አረጋዊ በርሄ መለስ እና ስብሃትን የሚተችበት እድል ካገኘ ብቅ ይላል። በተረፈ ብዙም የለም። ስርአቱን የሚያውቁት እንደመሆኑ ብዙ ማገዝ በቻሉ ነበር። ምናልባት አቻችለው መጓዝ ይፈልጉ ይሆናል። ግንባር መስመሩ ላይ አሉ ማለት ግን አይቻልም። ስለዚህ የትም የሉም… 

ነጋሶ – በየነ- መረራ….?

በየነና መረራ ሸክማቸውን ስዬ አብርሃ ላይ ጭነው እረፍት የፈለጉ መስለው ታይተዋል። በየነ ጴጥሮስ ፕሬዚዳንት ግርማን ለመተካት ሞክሮ ከከሸፈበት ወዲህ ተስፋ ቆርጦአል። መረራ በንግግሩ ለወያኔ ጩቤ ቢሆንባቸውም፣ አሁን አሁን የአፍእላፊ ክሱን በመስጋት ቃላት በመምረጥ ሲጨናነቅ ይታያል። በፍርሃት ማሰሮ ውስጥ ተጨረማምቶ መቀመጥ ግዴታው የሆነ ፖለቲከኛ ምን አይነት ትግል ማድረግ ይቻለዋል? በርግጥ ጊዮርጊስ ከፈቀደ ሁለቱ አንጋፋዎች ወደፊት ሚኒስትር የመሆን እድል ይኖራቸው ይሆናል። መለስን ይተካሉ ብሎ የሚጠብቅ ግን ያለ አይመስልም። 

ነጋሶ የዋህ ናቸው። የቅርብ የትግል ጓዳቸው አንዷለም አራጌ ታስሮ በጡጫና በእርግጫ ሲደበደብ እሳቸው፣ “በአንቀፅ 22 መሰረት..” የሚል አረፍተ ነገር ያለበት መግለጫ ሰጡ። ኢትዮጵያ ላይ ምን አንቀፅ አለ? ሌላው ቀርቶ አንቀፅ 39 እንኳ፣ ለህወሃት ስትራቴጂአዊ ፍላጎት ብቻ ተብሎ የገባ ነው። ዶክተር ነጋሶ አንቀፅ 22ን ከሚጠቅሱ፣ የብሉይ ኪዳን ህግን ቢጠቅሱ በተሻለ ነበር። ማለትም፣ “ለእርግጫ – እርግጫ! ለጡጫ – ጡጫ!” የሚለውን። ነጋሶ የወያኔን ህገመንግስት ያረቀቁት ከልባቸው ስለነበር፣ አሁንም ህጉ በስራ ላይ ያለ ይመስላቸዋል። ነጋሶ ይህን ያህል ዘመን ከህወሃት ጋር አብረው ሰርተው፣ የህወሃትን አንጎልና ልብ አለማወቃቸውን ሳስበው ግርም ይለኛል። የሆነው ሆኖ ነጋሶ ጊዳዳ ኢትዮጵያን ከመምራት አንፃር አማራጭ ናቸው ብዬ አላስብም።  ታሪክ ግን፣ “ሰላምተኛ እና ጥሩ ሰው ነበሩ” በሚል ያስታውሳቸው ይሆናል።

ታማኝ በየነ…?

ታማኝ ኮሜዲያን በነበረበት ጊዜ በጣም ያስቀን ነበር። ከመነሻውም ግን ቀልዶቹ ፖለቲካ የተርከፈከፈባቸው ነበሩ። በተፈጥሮው በነፃነት የመናገር ተሰጥኦ ስላለው በዘመነ ደርግም ቢሆን፣ ከሌሎች ይልቅ ልቆ ደፍሮ ፖለቲካውን ይነካካ ነበር። ፖለቲካ በቀልድ ሲቀርብ አጥንት ይሰብራል። እንደ ታማኝ ፖለቲካዊ ኩመካ ቢሆን የወያኔ አጥንቶች ከመሰባበር አልፈው ዱቄት መሆን ነበረባቸው። ታማኝ ኩመካውን በመተው ወደ ፖለቲካው ከገባ ወዲህ ብዙ ፈተናዎች ገጥመውታል። አንዳንድ ወዳጆቹ ጠጋ ብለው፣

“ታማኝ! ፖለቲካውን ትተህ ወደ ሙያህ ብትመለስ ይሻልሃል። የሚያምርብህ ኩምክናው ነው” ብለውታል። አንድ ዘመዱ ደግሞ፣ “…ስትናገር አዝማሪ ነኝ ትላለህ። እኛ በዘራችን አዝማሪነት የለብንም። ለምን ስማችንን ታጠፋለህ?” ሲል ጠይቆታል። ቀልድ ሊሆን ይችላል። “ፕሮፌሰርና ዶክተር መውቀስ ታበዛለህ” እያሉ የሚተቹት የመኖራቸውን ያህል፣ “ፕሮፌሰርና ዶክተር ከሚባሉት አንተ ትሻላለህ።” እስከማለት የሚሄዱም አሉ። ደግነቱ ታማኝ በትችቱም ሆነ በሙገሳው የሚሞቀውም ሆነ የሚበርደው አይነት አይመስልም። ባለ አዞ ቆዳ ነው። እንደልቡ ይናገራል። ጠላቶቹም ወዳጆቹም ጓጉተው ያዳምጡታል። “የኔ እውነቶች” የሚለው አባባል አለው። በርግጥ አስቦ ከሚናገረው ይልቅ፣ በስሜት ከልቡ የሚያፈልቀው ይበልጥ ሳቢ ነው። 

የታማኝ ፈተና የወያኔ ውግዘትና የጥራዝ ነጠቆች ትችት ብቻ አይደለም። ቱባ የሚባሉ ሰዎችን በፖለቲካው ለማነሳሳት በሚያደርገው ጥረት ብዙ ፈተና ይገጥመዋል። ታማኝ ቀረብ እያለ ወደ ስብሰባ ወይም ወደ ተቃውሞ ሰልፍ እንዲወጡ ሲጠይቃቸው እንዲህ የሚል ምላሽ የሚሰጡት አሉ፣

“አዲሳባ ላይ ቤት መስራት ጀምሬያለሁ። በቪዲዮ የምታይ ከሆነ አስቸጋሪ ነው። ሊተናኮሉኝ ይችላሉ። በአሳብ ግን አብሬያችሁ ነኝ። ለማንኛውም ሞት ለወያኔ!”ሌሎች ደግሞ፣“ምን መሰለህ ታማኝ!? በዚህ ገፈርሳ አካባቢ መሬት ወስጃለሁ። ለዶሮ እርባታ ነው ያሰብኳት። አጥሯን አጥሬ እስክጨርስ ገለል ማለት ይሻላል። የምትሰሩትን ግን እደግፋለሁ። በርቱ! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!”

በርግማን ወያኔ የሞሞት ቢሆን ኖሮ ቀብሩ ገና ድሮ በተፈፀመ። በምርቃት ኢትዮጵያ ለዘልአለም መኖር ብትችልም ይህ ሁሉ ድካም ባላስፈለገ። መቼም እንዲህ ካሉ ፎጋሪዎች ጋር ተባብሮ ወያኔን ማስወገድ ህልም ነው። ታማኝ እንዲህ ባሉ ሰዎች ተከቦ፣ መንፈሱ ባለመርገቡ አደንቀዋለሁ፣ አዝንለታለሁም።

በርግጥ ታማኝ ‘ፖለቲከኛ ነኝ’ ብሎ አያውቅም። ርግማን ሆኖብን እንጂ ታማኝ ጊዜውን በፖለቲካ ጉዳይ ማባከን አልነበረበትም። ይቺ “የተረገመች” አገር ተሳክቶላት የሰው ልጅ እንደ ሰው የሚከበርባት አገር ለመሆን ከበቃች ግን፣ መጪው ትውልድ ታማኝን ወደ ነፃነት በሚያመራው መንገድ ላይ እንደ መንገድ ጠራጊ ያስታውሰው ይሆናል…  

ዳውድ እና ዱጋሳ…?

የዳውድ ኢብሳና የዱጋሳ በከኮን ኦነግ በሩቅ አጣምሮም ሆነ ለያይቶ ማየት ይቻል ይሆናል። ልዩነታቸውን አቻችለው የቀድሞውን ጠንካራ ኦነግ ወደ ነበረበት ለመመለስ እየሰሩ መሆኑ ይሰማል። የሽማግሎዎችና የወጣት ኦሮሞዎች ግፊት አለበት። “የአንድነት ሃይሎች” ዳውድ ኢብሳን አክራሪ ይሉታል። ለረጅም ጊዜ የኦነግ ሰራዊት ኮማንደር የነበረውን ዱጋሳ በከኮን ቢያውቁት ኖሮ ግን ዳውድን ያመሰግኑት ነበር። ዞሮ ዞሮ ይህ ነባሩ የኦነግ ሃይል እንደገና ተሰብስቦ፣ አንድ ሃይል መፍጠር ከቻለ በቀጣይዋ ኢትዮጵያ ላይ ተፅእኖ የማሳደር አቅሙ ቀላል አይሆንም። ባለፉት 20 አመታት ከቋንቋ እና ኦሮሚያን ክልል ከመመስረት አንፃር የተሰሩ በጎ ስራዎች በኦነግ ግፊት የተፈፀሙ ናቸው። በመሆኑም የኦሮሞ ህዝብ ስነልቦና ከኦነግ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ከመለስ ስልጣን መልቀቅ ጋር ተያይዞ የኦሮሞ ህዝብ በኦነግ ዙሪያ ሊሰለፍ መቻሉን ማስቀረት የሚቻል አይመስልም። እናም ዳውድና ዱጋሳን በአእምሮ ውስጥ መያዙ የግድ ይላል።

ሃይለማርያም ደሳለኝ….?
ሌላው አማራጭ ራሱ ወያኔ ነው። ኢትዮጵያ የተባለችው አገር በመለስ ዜናዊ እጅ ላይ ያለች አገር እንደመሆኗ ወያኔ፣ “ጥፋ ከዚህ” የሚባልና በቀላሉ የሚገፈተር ሃይል አይደለም። ስልጣን፣ ጠመንጃ፣ ገንዘብና ተንኮል የታጠቀ አደገኛ ሃይል ነው። መለስ እስከ 2015 የአባይ ግድብን በማጠናቀቅ፣ የአዲስአበባን የከተማ ባቡር በማስመረቅ፣ የኑሮ ውድነቱን መቀነስና ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ከቻልን እስከ 2030 ስልጣን በእጃችን ይሆናል” እያለ አባላቱን እየሰበከ ይገኛል። በግልባጩ ህወሃት ውስጥ ውስጡን ያልተረጋጋና በቋፍ ላይ ያለ ቡድን መሆኑን ማመን አይፈልግም። የኢኮኖሚ እድገት ቢኖር እንኳ፣ የመብትና የነፃነትን መገፈፍን ሊተካ አይችልም። የሰው ልጅ ለክብሩ እንጂ ለሆዱ አይኖርም። መለስ የመብትና ዴሞክራሲ ጥያቄውን ዘግቶ ሃይለማርያምን በሞግዚትነት ለማንገስ ተዘጋጅቶአል። “ይህን ከማድረግ ሊያስቆመን የሚችል ሃይል የለም” ብሎም ያምናል። በርትተው ሊቃወሙ የሚችሉትን ግለሰቦች ሁሉ በካሮትና ዱላ ስልት ለመቆጣጠር ሙከራውን ቀጥሎአል። እንግዲህ የመለስ የመጀመሪያ ምርጫ ሃይለማርያም ሊሆን ቢችልም፣ ሃይሌ በእግሩ መቆም አቅቶት እንዳይንገዳገድ እነ ደብረፅዮንና ቴዎድሮስ አድሃኖም ታኮ ሆነው ያገለግሉታል። እስከ 2030? ምን ችግር አለው? ህልም ማለም አይከለከልም…

ያልታወቁ ወጣቶች….?

የመለስ ዜናዊን ስልጣን ሊረከቡ የሚችሉ ወጣቶች ወደፊት እየመጡ ይሆን? በቅንጅት የብርቱካን አብዮት ወቅት፣ ትንታግ የነበሩ ወጣቶች አበባማው አብዮቱ ከከሸፈ በሁዋላ አብዛኞቹ ተሰደዋል። የኦነግ ወጣት አባላትም እንዲሁ መሪዎቻቸውን ተከትለው ኮብልለዋል። ህዝብ ግን በርግጥ ተስፋ አይቆርጥም። እንደገና አምጦ ታጋዮችን ይወልዳል። ማን ያውቃል? ገና ያላወቅናቸው የአገር ተስፋዎች ይኖሩ ይሆናል። ምናልባት በኢህአዴግ መዋቅር ውስጥ ያደፈጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ምናልባት ደግሞ በሰራዊቱ ውስጥ ያሉ መስመራዊ መኮንኖች! ምናልባት በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ሶስት ሆነው የሚመካከሩ ሻለቆችና ሻምበሎች ይኖሩ ይሆን? እነዚህ ያልታወቁ ወጣቶች ከቶ እነማናቸው? ምናልባት ከትግራይ ይነሱ ይሆን? 

በመጨረሻ….?

በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሰላማዊ ፖለቲከኞች ምንም ማድረግ እንደማይችሉ በተደጋጋሚ የታየ ቢሆንም፣ ዞሮ ዞሮ ትግሉ መካሄድ ያለበት ከውስጥ መሆኑ ይታመናል። ርግጥ ነው፣ ልክ እኔ እንደማደርገው እንዲህ ደጅ ሆኖ መለፍለፍ ቀላል ነው። በቀለ ገርባ፣ እስክንድርና አንዷለም ጫማ ውስጥ መግባት ግን እጅግ ከባድ ሊሆን ይችላል። እየወደቁ ወደፊት ከመግፋት በቀር ግን ምርጫ የለም። ያም ሆኖ የእርቅ መንፈስ አስፈላጊነት መቼም ቢሆን ጊዜው አያልፍበትም። ከ50 አመታት በሁዋላ አሁን ስለፖለቲካ የምናወጋው አንዳችንም በህይወት አንኖርም። ተጠራርተንና ተጠራርገን እንወገዳለን። ምን ይሆን ለቀጣዩ ትውልድ ትተንለት የምናልፈው? ቂምና ጥላቻ? የማያባራ ጦርነት? ቅጥፈትና ሌብነት? ሃሜትና ቡጨቃ? ከቶ ምን ይሆን? በመጨረሻ ከተጠቀሱትና ካልተጠቀሱት መካከል “በቀጣይ ኢትዮጵያን የሚመራት ማነው?” የሚለው ጥያቄ በርግጥ አሁንም አልተመለሰም። ሆኖም “የነገው ቀን” በፍጥነት ወደ እኛ እየገሰገሰ ስለሆነ፣ መለስን ማን እንደሚተካ በቅርቡ እናውቀው ይሆናል…        

 
የቅዳሜ ማስታወሻ ተስፋዬ ገብረአብ 

ወያኔ ተጨናንቆአል? 

ርግጥ ነው ሰሞኑን ወያኔ በጣም ተጨናንቆአል። ለአመፅ እርሾ ሊሆኑ በሚችሉ ቁጣዎች ተከበዋል። የሶማሊያ ተልእኮ እየከሸፈ ነው። አልሸባብ እያሸመቀ ደጋግሞ አደጋ መጣሉን በመቀጠሉ፣ ከዚህ በላይ ሶማሊያ መቆየት እንደማይችሉ ተረድተው ጓዛቸውን መሸከፍ ይዘዋል።  ከኤርትራ ጋር የጀመሩት የጦርነት ድራማ፣ ላይ ላዩን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ እንደሚያውሉት አለመሆኑ ተባኖበታል። የውስጥ ቀውሱ ተባብሶአል። የመምህራን አመፅ ወዴት እንደሚያመራ አልታወቀም። ቢታፈንም መልኩን ቀይሮ መከሰቱ የማይቀር ነው። ወያኔ ሙስሊሙን ለመከፋፈል ያደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ግማሽ አካል የሆነው ሙስሊሙ የህብረተሰብ ክፍል ከወያኔ ጋር ተፋጦአል። ወያኔ መውጪያው ቀዳዳ ጠፍቶታል። የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን ነባር ቅርሶች የማውደሙ ሴራ አማኙን ህዝብ ያሸማቀቀና ያስደነገጠ ሆኖአል። ገና አልተቋጨም። ከደቡብ ክልል የተፈናቀሉት አማሮች ጉዳይ፣ ሊታፈን ባለመቻሉ ፈንድቶ ወጥቶአል። የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱንም ሊቆጣጠሩት አልቻሉም። ሙስናው ጣራ ነክቶአል። ስርቆቱ፣ “ተከተል አለቃህን” የሚል ስያሜ አጊኝቷል። የህወሃት ወገኖች የቅንጦት ህይወት ይሉኝታ አጥቶአል። እና በዙሪያቸው ያለውን የተቆጣ የህዝብ አይን ለማፈን መጨነቃቸውን ማስተዋል ይቻላል። አፈና ግን መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ምርጫው አንድ ብቻ ነው። ከራስ ጋር እና ከእውነታው ጋር መታረቅ!    
የቅዳሜ ማስታወሻ ተስፋዬ ገብረአብ 

እኛና የኛ ከብቶች 
ሰሞኑን የሚገርም ዜና ሰምቼ ነበር። ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ የከብቶችን ከብታዊ መብት አያያዝ መብት ለማስከበር ህግ እንደሚረቅ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በይፋ ማሳወቃቸው ነው። ይህን ህግ ለማርቀቅ የተገደዱትም በአንደኛው አለም የሚኖሩ ዜጎች፣ “ከብታዊ አያያዛቸው ጥሩ ያልሆነ ከብቶችን ስጋ አንመገብም” ማለት በመጀመራቸው፣ የኢትዮጵያን የስጋ ኤክስፖርት ገበያ እንዳይጎዳ’ ነው ተብሏል። 
ለመሆኑ በዚህች አለም ላይ ጥሩ ከብታዊ ህይወት አሳልፎ የሚሞተው የኛ ከብት ነው ወይስ የምእራቡ አለም ከብት?  
እኔ በግሌ የአበሾችንም ሆነ የአውሮፓውያንን ከብቶች ህይወት በቅርብ የማየት እድል ገጥሞኛል። የወተት እና የቅቤ አገር ከተባለችው ሆላንድ ገጠር ውስጥ ነዋሪ ነኝ። በአይኔ በብረቱ እንዳየሁት ከሆነ የአውሮፓ ከብቶችን “ከብት” ከማለት “ዛፍ” ማለት ይቀላል። ምክንያቱም እዚያው በቆሙበት ይበላሉ። እዚያው በቆሙበት ይፀዳዳሉ። እዚያው በቆሙበት አርግዘው፣ ወልደው ይታለባሉ። የሚወልዱት አምጠው ሳይሆን በቢላ ተቀደው ነው። ጥጆቻቸው ወንድ ከሆኑ፣ “የጥጃ ስጋ” እየተባሉ ይታረዳሉ። ወደዱም ጠሉ ጡታቸው በማሽን ሃይል ምጥጥ ተደርጎ ይታለባል። በጥቅሉ የአውሮፓ ከብቶች ከብትነታቸውን ተነጥቀው ዛፍ ሆነዋል። የከብቶች መብት መጠበቅ ካለበት፣ የአበሻ ከብት መብት ሳይሆን፣ የምእራቡ አለም ከብቶች መብት ጉዳይ ቢታሰብበት ይመረጣል። 
እንነጋገር ከተባለ በዚህች አለም ላይ እንደ አበሻ ከብት ተንቀባሮ የሚኖር ከብት አለ እንዴ?  
የኛ ከብቶች ማለዳ ተነስተው በርግጥ ይታለባሉ። ጥጃዋ ካልጠባች ግን ወተት ስለማይሰጡ፣ ሰው እና ጥጃ ወተቱን እኩል ነው የሚካፈሉት። ከዚያም ለግጦሽ እና ውሃ ለመጠጣት ይሰማራሉ። እየተዘፈነላቸው፣ ዋሽንት እየተነፋላቸው፣ ጆሮአቸው ላይ በተበሳ ቁጥር ሳይሆን፣ በስማቸው እየተጠሩ ህይወትን ይገፉዋታል። ከበሉ ከጠጡ በሁዋላ ደግሞ ሁዳዱ ላይ እየዘለሉ ይጫወታሉ። ወይፈኑ፣ ከአብሮ አደጉ ጊደር ጋር በጠራ ፀሃይ ይዝናናል። ሲጠግቡ ወይፈን ከወይፈን ጋር የሞት ሽረት የቀንድ ውጊያ ያካሂዳሉ። በርግጥ በእርሻ ጊዜ በሬው ድካም አለበት። ዘፈን ግን በጆሮው ይንቆረቆርለታል። ከገበሬም ጋር አብረው ነው የሚደክሙት። ሲመሽ እያወጉ ወደ ጎጆአቸው ያመራሉ። የገበሬ ልጆችና፣ የበሬ ጥጆች እየተሳሳሙ አብረው አንድ ክፍል ውስጥ ያድራሉ። እበታቸውን ሲጥሉ፣ ቁና የያዙ ህፃናት እበቱ መሬት ዱብ ከማለቱ በፊት ይቀበሏቸዋል። 
ለመሆኑ እንደ አበሻ ከብት፣ እውነተኛውን የከብት ህይወት የሚኖር ከብት በአለም ላይ አለ?  
የአበሻ ጥጃ ታርዶ አያውቅም። እንደ ሰው ልጅ አድጎ፣ ለወግ ማእረግ በቅቶ፣ አርሶ፣ ወልዶ በመጨረሻ “ሰው ከሞት፣ ከብት ከቢላ” አያመልጥምና ይታረዳል። የኛ ከብቶች ከብታዊ መብት የተደፈረው የት እና መቼ ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ከብቶች በዱላ ይደበደባሉ እንዴ? ሰምቼ አላውቅም። እርሻ ላይ በሬ ሲለግም በጅራፍ ሾጥ ይደረጋል። ጅራፍ የበሬ ቆዳን አይጎዳውም። ጥጃና ላም ሲደበደብ ግን አይቼም ሰምቼም አላውቅም። አልፎ አልፎ አንዳንድ ባለጌ ህፃናት፣ በድንጋይ ቀንዳቸውን ይመቷቸዋል። በተረፈ ግን ጥጃ ሲሳም፣ ላምና በሬ ሲዘፈንላቸው ነው የማውቀው። እና የመለስ ዜናዊ መንግስት ከምን ተነስቶ ነው የከብቶችን መብት አያያዝ ለማሻሻል እንዲህ ታጥቆ የተነሳው?   ይልቁን የከብቶቹን አቆይተን፣  እስርቤት ውስጥ ስለሚደበደቡ ሰዎች መነጋገር አይሻልም?

     

የቅዳሜ ማስታወሻ ተስፋዬ ገብረአብ 

እኛና የኛ ከብቶች 
ሰሞኑን የሚገርም ዜና ሰምቼ ነበር። ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ የከብቶችን ከብታዊ መብት አያያዝ መብት ለማስከበር ህግ እንደሚረቅ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በይፋ ማሳወቃቸው ነው። ይህን ህግ ለማርቀቅ የተገደዱትም በአንደኛው አለም የሚኖሩ ዜጎች፣ “ከብታዊ አያያዛቸው ጥሩ ያልሆነ ከብቶችን ስጋ አንመገብም” ማለት በመጀመራቸው፣ የኢትዮጵያን የስጋ ኤክስፖርት ገበያ እንዳይጎዳ’ ነው ተብሏል። 
ለመሆኑ በዚህች አለም ላይ ጥሩ ከብታዊ ህይወት አሳልፎ የሚሞተው የኛ ከብት ነው ወይስ የምእራቡ አለም ከብት?  
እኔ በግሌ የአበሾችንም ሆነ የአውሮፓውያንን ከብቶች ህይወት በቅርብ የማየት እድል ገጥሞኛል። የወተት እና የቅቤ አገር ከተባለችው ሆላንድ ገጠር ውስጥ ነዋሪ ነኝ። በአይኔ በብረቱ እንዳየሁት ከሆነ የአውሮፓ ከብቶችን “ከብት” ከማለት “ዛፍ” ማለት ይቀላል። ምክንያቱም እዚያው በቆሙበት ይበላሉ። እዚያው በቆሙበት ይፀዳዳሉ። እዚያው በቆሙበት አርግዘው፣ ወልደው ይታለባሉ። የሚወልዱት አምጠው ሳይሆን በቢላ ተቀደው ነው። ጥጆቻቸው ወንድ ከሆኑ፣ “የጥጃ ስጋ” እየተባሉ ይታረዳሉ። ወደዱም ጠሉ ጡታቸው በማሽን ሃይል ምጥጥ ተደርጎ ይታለባል። በጥቅሉ የአውሮፓ ከብቶች ከብትነታቸውን ተነጥቀው ዛፍ ሆነዋል። የከብቶች መብት መጠበቅ ካለበት፣ የአበሻ ከብት መብት ሳይሆን፣ የምእራቡ አለም ከብቶች መብት ጉዳይ ቢታሰብበት ይመረጣል። 
እንነጋገር ከተባለ በዚህች አለም ላይ እንደ አበሻ ከብት ተንቀባሮ የሚኖር ከብት አለ እንዴ?  
የኛ ከብቶች ማለዳ ተነስተው በርግጥ ይታለባሉ። ጥጃዋ ካልጠባች ግን ወተት ስለማይሰጡ፣ ሰው እና ጥጃ ወተቱን እኩል ነው የሚካፈሉት። ከዚያም ለግጦሽ እና ውሃ ለመጠጣት ይሰማራሉ። እየተዘፈነላቸው፣ ዋሽንት እየተነፋላቸው፣ ጆሮአቸው ላይ በተበሳ ቁጥር ሳይሆን፣ በስማቸው እየተጠሩ ህይወትን ይገፉዋታል። ከበሉ ከጠጡ በሁዋላ ደግሞ ሁዳዱ ላይ እየዘለሉ ይጫወታሉ። ወይፈኑ፣ ከአብሮ አደጉ ጊደር ጋር በጠራ ፀሃይ ይዝናናል። ሲጠግቡ ወይፈን ከወይፈን ጋር የሞት ሽረት የቀንድ ውጊያ ያካሂዳሉ። በርግጥ በእርሻ ጊዜ በሬው ድካም አለበት። ዘፈን ግን በጆሮው ይንቆረቆርለታል። ከገበሬም ጋር አብረው ነው የሚደክሙት። ሲመሽ እያወጉ ወደ ጎጆአቸው ያመራሉ። የገበሬ ልጆችና፣ የበሬ ጥጆች እየተሳሳሙ አብረው አንድ ክፍል ውስጥ ያድራሉ። እበታቸውን ሲጥሉ፣ ቁና የያዙ ህፃናት እበቱ መሬት ዱብ ከማለቱ በፊት ይቀበሏቸዋል። 
ለመሆኑ እንደ አበሻ ከብት፣ እውነተኛውን የከብት ህይወት የሚኖር ከብት በአለም ላይ አለ?  
የአበሻ ጥጃ ታርዶ አያውቅም። እንደ ሰው ልጅ አድጎ፣ ለወግ ማእረግ በቅቶ፣ አርሶ፣ ወልዶ በመጨረሻ “ሰው ከሞት፣ ከብት ከቢላ” አያመልጥምና ይታረዳል። የኛ ከብቶች ከብታዊ መብት የተደፈረው የት እና መቼ ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ከብቶች በዱላ ይደበደባሉ እንዴ? ሰምቼ አላውቅም። እርሻ ላይ በሬ ሲለግም በጅራፍ ሾጥ ይደረጋል። ጅራፍ የበሬ ቆዳን አይጎዳውም። ጥጃና ላም ሲደበደብ ግን አይቼም ሰምቼም አላውቅም። አልፎ አልፎ አንዳንድ ባለጌ ህፃናት፣ በድንጋይ ቀንዳቸውን ይመቷቸዋል። በተረፈ ግን ጥጃ ሲሳም፣ ላምና በሬ ሲዘፈንላቸው ነው የማውቀው። እና የመለስ ዜናዊ መንግስት ከምን ተነስቶ ነው የከብቶችን መብት አያያዝ ለማሻሻል እንዲህ ታጥቆ የተነሳው?   ይልቁን የከብቶቹን አቆይተን፣  እስርቤት ውስጥ ስለሚደበደቡ ሰዎች መነጋገር አይሻልም?

     

የቅዳሜ ማስታወሻ ተስፋዬ ገብረአብ 

ስዬ አብርሃ (ቃለመጠይቅ) – EMF 
ጥያቄ – ፌዴራል ፖሊስን በሚመለከት ለቀረበው ጥያቄ መልስ –

አቶ ስዬ አብርሃ – የሲቪል ፖሊስ እና የፌዴራል ፖሊስ የተለያዩ ናቸው። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፌዴራል ፖሊስ ፓራ ሚሊተሪ ነው። ተቃውሞን በሃይል ለመደምሰስ የተቋቋመ ነው።

ጥያቄ -የአረብ አገሮችን አብዮት በተመለከተ –

አቶ ስዬ አብርሃ- በአረብ አገር ህዝቡ ፍርሃትን አሸንፏል። – የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ መከራ አይቷል። የኛ ትውልድ በቀይ ሽብር ተመቷል። እኛ አባቶች ሆነናል። በ1997/2005 የተነሳው እንቅስቃሴ ህዝቡ እንደገና ህዝቡ ፍርሃትን ሰብሮ ወጥቶ ነበር። በወቅቱ ያየውን ግድያ ሲመለከትና ነገሩ ወደ ቀይ ሽብር ማህጸን ሲገባ ወላጆች ፡ተዉ ይሄ ነገር አያዋጣም” ማለት ጀምሯል። ይህ ግን ጊዜያዊ ነው። የታመቀ ቁጣ፤ በቃ ብሎ ሲነሳ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መልክ ይቀየራል።

ጥያቄ – ስለፓርቲዎች ብዛት ስለተነሳው ጥያቄ –

አቶ ስዬ አብርሃ – ኢህአዴግ እሱ የሚፈልጋቸው ፓርቲዎች አሉ። እንዲቆዩ የሚፈልጋቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች እያባበለ ይዟቸው ይቆያል። ወቅቱ ሲደርስ ይጠቀምባቸዋል። ለምሳሌ አሁን ለዚህ አመት የወረዳ ምርጫ 12 ሚሊዮን ተፈቀደ። ኢህ አዴግ 9 ሚሊዮን ወሰደ። አንድ ሚልዮን ለኢህ አዴግ አጋር ድርጅቶች ተሰጠ። ለአንድነት ፓርቲ 3 ሺህ 500 ነው የተሰጠው። እንዲህ አይነት ጨዋታ ነው ያለው። ስለዚህ ኢህአዴግ የሚፈለፍላቸው የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምረን ከቆጠርን ስልሳ እና ሰባ ቢደርሱ ሊገርመን አይገባም።

ጥያቄ- አሁን ያሉትን ወታደሮች ቅረቧቸው ብለዋል። የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊትን በተመለከተ ምን ይላሉ?

አቶ ስዬ አብርሃ — የቀድሞ ወታደሮች ያንን አስከፊው ዪሰፓ ስር አት ምርኩዝ እንዲሆን በመከላከያ ስር ወይም ተገደው ወይም ተቀጥረው፤ በገዛ ወገናቸው ላይ ጦርነት የከፈቱ፤ የሰሩ ናቸው። ጠላት ናቸው ወይ? ከተባለ፤ አይደሉም። ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ጥፋት ተፈጽሟል። ወታደር በጦር ውጊያ ይገላል፣ ይገደላል፤ ይማረካል። ወደ ራሱ ግንባር መሄድ ከፈለገም በአስር ሺዎች ተማርከው፤ በአስር ሺዎች የሚለቀቁበት ጊዜ ነበር። በመጨረሻም ደርግን አንዋጋም ያሉት እነዚሁ ወታደሮች ናቸው።

ጥያቄ- ኢህ አዴግ የሚለውን ስያሜ እንዴት ያዩታል?

አቶ ስዬ አብርሃ -አንድ ሰው ስሙ ገብረ እግዚአብሄር ከሆነ ገብረ እግዚአብሄር ነው የምንለው። ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ጥቅም ያስጠብቃል ወይ? ካልን አያስጠብቅም ነው መልሱ።

ጥያቄ- ህወሃት በኢህ አዴግ ላይ የበላይነት አለው ለሚለው ጥያቄ –

አቶ ስዬ አብርሃ – ኦህዴድ ወይም ብአዴን የሚለው ነገር ምርጫ ለመስረቅ ካልሆነ በቀር፤ የሚያስፈልጉ ድርጅቶች አይደሉም። በአጠቃላይ ህወሃት የመስራች ወይም የአባላቱ ፓርቲ አይደለም። እባካችሁ የትግራይም አትበሉ። የቤተሰብ ፓርቲ እየሆነ ነው። ከዚያም እየቀጠነ የመለስ እና የሚስቱ የአዜብ ፓርቲ እየሆነ ነው ያለው።

ጥያቄ-ከህወሃት መስራቾች መካከል አንዱ የጎንደር ልጅ ነው ምንም ብላችሁ አታውቁም። እርስዎ ምን ይላሉ?

አቶ ስዬ አብርሃ – ማነው መስራች? የሚለው በራሱ አከራካሪ ነው። ለምሳሌ አስገደ ገብረስላሴ መስራች አይደለም የሚሉ አሉ። ነገር ግን መጀመሪያ በርሃ ላይ ከወጡት ሰዎች አንዱ ነበር። ከዚያ ውጪ ጎንደሬ ስለሆነ ከመስርቾች አንዱ ነው ወይም አይደለም የተባለበትን ታሪክ አላውቅም። እኔ የማውቀውን ልናገር። እኔ መጀመሪያ የማውቀው ወንድወሰን ከበደን ነው። የሰላሌ ኦሮሞ፤ የሸዋ ተወላጅ ነው። በስልሳዎቹ ህወሃትን ተቀላቅሎ፤ ትግሪኛ ለምዶ የማዕከላዊ ፓርቲው አባል ሆኖ አዲስ አበባ እስከምንገባ ድረስ አብሮን ሰርቶ ነበር። በኋላ ግን ያለ ፍላጎቱ ይመስለኛል ወደ ብአዴን ገብቶ እንዲሰራ ተደርጓል። አሁንም በህይወት አለ።

ጥያቄ – የኢህአፓው ደብተራውን በተመለከተ ምን የሚያውቁት ነገር አለ? ህወሃት ገድሎታል? በህይወት አለ? ማወቅ እንፈልጋለን –

አቶ ስዬ አብርሃ -ይሄ በህወሃት እና በ ኢህ አፓ መካከል የተደረገው ጦርነት መደረግ ያልነበረበት ጦርነት ነው። ይሄ የታሪካችን አንዱ መጥፎ ገጽታ ነው። እኔ እና አቶ ግርማዬ አንድ ቦታ ላይ በተለያየ ግንባር ሆነን ተታኩሰናል። ብዘት ላይ ነበር ውጊያው የተካሄደው። መጥፎ ውጊያ ነበር። በህወሃት በኩል የነበረውን ጦርነት የመራሁት እኔ ነኝ። አቶ ግርማዬ ግዛው ደግሞ በኢህ አፓ ወገን ሆነው ወግተውናል። አሁን ደግሞ አብረን አንድ መድረክ ላይ ለአንድ ፓርቲ አብረን እየሰራን ነው።

እኔ የማውቀው ነገር ቢኖር እናገር ነበር። ከዚያ በላይ እኮ ብዙ ሰዎች ሞተውብናል። ይሄ ለምንድነው ቁርሾ የሚሆንብን? እኔም የወደቁ በግፍ የተገደሉ ጓደኞች አሉን። እነዚህን ሰዎች ብናነሳ ገመድ መጓተት ነው የሚሆነው። ለማንም አይጠቅምም። ወደፊት እንደገና ይሄንን ቁርሾ እያነሳን እየተጨቃጨቅን መኖር የለብንም።

እኛ የናንተን ሬሳ ተሻግረናል፤ እናንተም የኛን ሬሳ ተሻግራችሁ አልፋችኋል። እናንተን በመግደል ጀብዱ አድርገናል። እናንተም እኛን ገድላችሁ ደስ ብሏችሁ ነበር። ነገር ግን ስህተት ነበር። የኛ ትውልድ ጥፋት ሰርቷል። ይካስ። ለአንድ ሰው አይደለም፤ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው የምናገረው። የኛ ትውልድ እርስ በርሱ ተላልቋል። አሁንም ቢሆን ሰዎች እየሞቱ ነው። የአንዷለምን ቅስም መስበር ሲያቅታቸው ጭንቅላቱን ለመስበር እየሞከሩ ናቸው። በዚህ የአርባ አመት ውስጥ ብዙ ስህተት ተሰርቷል።

ጥያቄ- ተስፋዬ ገብረአብ ስለ እርስዎ መጥፎ ነገር ይጽፋል። ምን ይላሉ?

አቶ ስዬ አብርሃ – ይሄንን ሰውዬ እኔ አላውቀውም፤ እሱ ግን ያውቀኛል። ስለኔ ይጽፋል። የላከው ይኖር ይሆናል። ሻዕቢያም እኮ ያብጠለጥለኛል። ሻዕቢያ የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ ሲመጣ፤ የለም ይሄ አይሆንም ብዬ ስለተዋጋሁ ይጠሉኛል። በፖለቲካ አለም ስትኖር ሁሉም ሰው ይወደኛል ማለት አይቻልም። ለምንድነው ይሄን የሚያደርገው አላውቀውም።

ጥያቄ- ትጥቅ ትግልን አስመልክቶ –

አቶ ስዬ አብርሃ – አሁን ባለው አለም አቀፍ አካሄድ ትጥቅ ትግል ማድረግ ያስከብራል ወይስ ተቀባይነት ያሳጣል። ለትግሉ የትኛው ነው ግርማ ሞገስ የሚሰጠው? ለመሞት ዝግጁ ከሆኑ አዲስ አበባ ሆነው ህዝብ እየታዘበ፤ ሰላማዊ ትግል ማድረግ ማድረግ ይቻላል። በአሁኑስ ወቅት፤ ማነው መንግስትን ለመጣል የሚያስችል መሳሪያ የሚሰጥህ? አለማዊ ግንኙነት ተቀይሯል። እናንተስ ደርግን ያሸነፋችሁት እንደዚያ አይደለም ወይ ልትሉ ትችላላችሁ? የዚያን ጊዜውና የአሁኑ የሰማይና የመሬት ያህል ልዩነት አለው። (ሰፊ ትንታኔ ተደርጓል)

ከዚያ በተረፈ የትጥቅ ትግል የሚያደርጉትን “እኔ ከናንተ ጋር የለሁበትም” እላለሁ እንጂ፤ ከመለስ ጋር ተባብሬ ይጥፉ አልልም። ሁላችንም ክንዳችንን አስተባብረን በሰላማዊ ትግል እንቀጥል እላለሁ።

ጥያቄ- የደርግን ሰራዊት አስመልክቶ– በደርግ ሰራዊት ላይ ያለዎትን አመለካከት አስተካክለው ቢገልጹልን።

አቶ ስዬ አብርሃ – እኔ ሰው እንዲያጨበጭብልኝ የማላምንበትን ነገር አልናገርም። የማላምንበትን ነገር ግን ሰው እንዲወድልኝ ብዬ አልናገርም። እኔ ሰው እንዲያምንልኝ እንጂ እንዲወደኝ አልጨነቅም። ለኔ ፖለቲካ እምነት ነው። በትግል ወደ ትግል ስገባም የማምንባቸው ነገሮች ስለነበሩ ነው። ሁሉም የሚጠላውን ጠልቼ፣ ሁሉም የሚወደውን ወድጄ አይደለም ህወሃትንም ሆነ አንድነት ፓርቲን የተቀላቀልኩት። በቅድሚያ ይሄ ግልጽ ይሁን።

ደርግ የኢሰፓን ፖለቲካ በሰራዊቱ ውስጥ ማስገባቱን እናውቃለን። (ሰፊ ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ) በጦር ሜዳም እያለን ለብዙ ጄነራሎች አክብርቶት ነበረኝ። አዲስ አበባ ከገባን በኋላ አንዳንዶቹን እያስጠራሁ አድናቆቴን ገልጬላቸዋለሁ። ጄ/ል ረጋሳ ጅማ አንዱ ናቸው። እኔ አዲስ አበባ ከገባን በኋላ በወቅቱ በሰራዊቱ ውስጥ የነበሩትን የተማሩ ሰዎች መልሰን እናስገባ ብዬ ተቃውሞ ደርሶብኝም ቢሆን ማድረግ ያለብኝን አድርጌያለሁ። በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ጦርነትም ወቅት ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶብኝም ቢሆን የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት አባላት መከላከያን እንዲቀላቀሉ አድርጌያለሁ።

ከዚያ በተረፈ የኔን ጓደኞች ገድለውም ቢሆን፤ ትልቅ ጀብዱ የፈጸሙትን፤ ገድለውም የሞቱትን ጨምር አከብራለሁ። ነገር ግን የደርግ ስርአት እና ሰራዊቱ የፈጸመውን በጠቅላላው ላደንቅ አልችልም፤ ተቃውሜው ነበር። አሁንም እቃወመዋለሁ።

ጥያቄ- የሃውዜንን እልቂት በተመለከተ… ሆን ተብሎ ህወሃት መረጃ ለደርግ ሰጥቶ ህዝቡን ያስፈጀበት ነው ይባላል። እስኪ እርስዎ እውነቱን ይንገሩን።

አቶ ስዬ አብርሃ – የሃውዜን ፍጅት የህወሃት ድራማ ነው ብለው የሚናገሩ ሰዎች አሉ። (በድንገት ስሜታዊ በመሆን፤ በቁጣ የተሰጠ መልስ ነበር)

እኛም እኮ ሰዎች ነን። ያንን ችግር ለመጋፈጥ በርሃ የገባነው እኮ ለሰዎች ህይወት ዋጋ ለመክፈል ነው። እንደዚያ አይነት የሃውዜን ፍጅት ላይ የተሳተፍን ቢሆን፤ ዛሬ እናንተ ፊት ቆሜ እንዴት በድፍረት እናገራለሁ። ሃውዜን የታወቀ የደራ ገበያ ነው። ሃውዜን ላይ የሞቱት የሁላችንም ወገኖች ናቸው። በቃ ሌላም ቦታ ደርግ ወገኖቻችንን እንደጨፈጨፈው ሃውዜንንም ደርግ ነው የጨፈጨፈው። ህወሃትን የምንወቅስበት ነገር አልቆብን ነው የሃውዜን እልቂት በህወሃት ላይ የምናላክከው።

አንድ ነገር እንድታውቁ እፈልጋለሁ። ብዙ ጥያቄዎች በህወሃት ስም ተጠይቄያለሁ። አሁን ከፊታችሁ ቆሜ የምናገረው ግን የህወሃት ተቃዋሚ ሆኜ፤ አንድነት ፓርቲን ወክዬ እንጂ፤ ህወሃትን ወክዬ አይደለም የምናገረው። ጭቅጭቃችን ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ነጻነት ይሁን። ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ እንነጋገር።

የቅዳሜ ማስታወሻ ተስፋዬ ገብረአብ 

ኢትዮጵያን ማን ይጠብቃት? ወታደር ወይስ መላእክት? 

  “…ኢትዮጵያ ጥንታዊ ብቻ ሳትሆን፣ በእግዚአብሄር እጅ የተሰራችና በአለም የመጀመሪያዋ አገር ናት። በእግዚአብሄር ጥበቃም ለዘልአለም እንደምትኖርና ዳግም ሃያል እንደምትሆን ማንም ጥርጥር አይግባው። ኢትዮጵያ አልፋ፣ ኢትዮጵያ ኦሜጋ ናት። በዚህ ዘልአለማዊ ጉዞ ውስጥ ደግሞ፣ አገሪቷን ከጥፋት የሚታደጓት መላእክት የመኖራቸውን ያክል፣ የእባቡን ድርሻ የሚወጡም ሞልተዋል…”

ይህ ከላይ ያለው አባባል የሰፈረው ኢትዮ ሚዲያ የተባለው ድረገፅ “ተስፋዬ ገብረ እባብ” በሚል ርእስ እኔን ባወገዘበት መጣጥፉ ነበር። መቸም አብርሃ አባቴን ጠምዶ ከያዘው አምስት አመታት አልፎታል። “አባቴን ልቀቀው” ብዬ በጓደኛው በጠበቃ ሼክስፒር ፈይሳ በኩል ብልክበትም ሊሰማ አልቻለም። አባታቸው ገብረአብ የሆኑትን እየፈለገ ያዛምደኛል። አሁን ደግሞ የትግል ስልቱን በመለወጥ፣ ገብረአብን – ገብረ እባብ አላት። የቃላት ሊቅ መኮኑ ነው። ከዚህ በፊትም ከማል ገልቹን “ከማል ገልቱ” ብሎ ፅፎ አንብቤያለሁ። “ተሳስቶ ነው” ልንል አንችልም። ራያ መሰረቱ ኦሮሞ እንደመሆኑ የኦሮምኛ ቃላት የሚቸግረው አይመስለኝም። ያለቀባቸው ፖለቲከኞች የቃላት ጥይት ይተኩሳሉ። ብርሃኑ ነጋን “ጨለማው መሸ” ብለውት ነበር። አንዳርጋቸው ፅጌን፣ “በትናቸው ፅጌ”። የኛ ዘመን ፖለቲካ! 

መለስ አገሪቱን ሸጦ እየጨረሰ አብርሃ በላይ ደግሞ… “አታስቡ ኢትዮጵያን የሚጠብቁ መላእክት አሉ” ይለናል። “ኢትዮጵያ በእግዚአብሄር እጅ የተሰራች” የሚለው ሙገሳም ለዚህ ዘመን አይሆንም። ጊዜውን ጨርሶ የተጣለ አባባል ነው። አገራት የሚሰሩት በሰዎች ነው። “ኢትዮጵያ በአለም የመጀመሪያዋ አገር” የሚለውም መሰረት የለውም። በየትኛው ጥናት ነው ይሄ የተረጋገጠው? ይሄ ሁሉ ማዘናጊያ ነው። ዜጎች አገራቸውን በወታደራዊ ሃይልና በፖለቲካ ማስጠበቅ አለባቸው። ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በተባለው የአባቶቼ ሃይማኖት መሰረት እግዚአብሄር ድንበር የማይገድበው የሰው ልጆች ሁሉ ፈጣሪ ነው። የድንበር ጉዳይ የሰው ልጆች ጣጣ ነው። የአገር ጉዳይ ከአምላክ ጋር የሚገናኝ አይደለም። የሰው ልጆች ውሳኔ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህን መሰል ቅስቀሳዎች ዜጎች ስለአገራቸው እንዳያስቡ፣ ሁሉን ለእግዚአብሄር ትተው ችላ እንዲሉ ያደርጋል። መለስ በእግዚአብሄር መኖር አያምንም። ሃገሪቱን እየሸጣት ነው። ዜጋ ዱላውንም ቁጣውንም መዞ “በቃህ” እስካላለ ድረስ፣ ኢትዮጵያን ከጥፋት የሚያድናት መልአክም ሆነ አምላክ የለም። የኢትዮጵያውያንን ጥንታዊ የአገር ፍቅር የአርበኛነት መንፈስ ለመስበር የቀረችው ብቸኛዋ እድል ሃይማኖት ሳትሆን አትቀርም!  

የቅዳሜ ማስታወሻ ተስፋዬ ገብረአብ 

መለስ ዜናዊ! ከሞት እንዴት እንዳመለጠ? 
ትረካውን ጥቂት አሰማምሬው ይሆናል እንጂ ይህ የምገልፅላችሁ ታሪክ በትክክል የተፈፀመ ነው።  ታሪኩን ካጫወተኝ ሰው ጋር ስናወራ፣

“ልፃፈው?” ስል ጠየቅሁት።

ሳቀ! በጣም ሳቀ! እና ፈቀደልኝ።

“ፃፈው! ድክመታችንን ያሳያል…” አለ። 
* * * 

ባጭር ጊዜ ውስጥ የታቀደ ነበር። በረቀቀ ጥበብም ሁኔታዎች ተስተካክለዋል። የቀረ ነገር ቢኖር በእቅዱ መሰረት መለስ ዜናዊ ላይ አደጋውን የሚጥል ደፋር ሰው ማግኘት ብቻ ነበር። የማጥቃት እቅዱን ለመፈፀም የታሰበው በጦር መሳሪያ አልነበረም። በቡጢ ነበር። አንድ ሃይለኛ ቡጢ! በቃ!

ቦታው ብራስልስ ነው። የአውሮፓ ህብረት ስብሰባ ላይ መለስ እንደሚገኝ ተረጋግጦአል። መረጃው አስተማማኝ ነበር። ለማስተማመኑ ማረጋገጫው መለስ ዜናዊ የሚቀመጥባት መቀመጫ ጭምር መታወቋ ነበር። የሆነው ሆኖ መለስ ላይ አደጋውን የሚጥል ሰው ለማግኘት ጥቂት ሰአታት ወስዶአል። ደግነቱ ከእቅዱ አዘጋጆች አንዱ፣
“እኔ እፈፅመዋለሁ! ደህና ቡጢ አቀምሰዋለሁ፣ ወይም አሰንብተዋለሁ!” አለ።
የዚህን ሰው እውነተኛ ስም መግለፅ አልፈልግም። ለትረካው እንዲያመቸኝ ግን ሙላቱ ብዬዋለሁ። ባጭሩ ደግሞ “ሙሌ!” እንለዋለን። እና ይህን ተግባር ለመፈፀም ሙሌ ሃላፊነቱን ወሰደ።
እነሆ! ዝግጅቱ ተጠናቆአል። ሙሌ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ጋዜጠኛ ሆኖ ይገባ ዘንድ የመግቢያ ወረቀት አጊኝቶአል። ካሜራ አንገቱ ላይ አንጠለጠለ። ግንባሩን ቋጠረ። ሙሌ ረጅም ሲሆን፣ እጁ ረጅምና እንደ ወይራ ጥምዝዝ ያለ ነበር። ከአዘጋጆቹ አንዱ መከረው፣
“ሙሉ ሃይልህን አታሳርፍበት። ዋናው መልእክታችንን ማስተላለፍ ነው” አለው።

ሙሌ በዚህ አልተስማማም።“ከሰነዝርኩማ እጠረምሰዋለሁ። ነካክቶ መተው አላውቅበትም”

ርግጥ ነው፣ መለስን አንድ ጥሩ ቡጢ ማቅመስ አለምን የሚያዳርስ ዜና ይሆናል። በተለይ ደግሞ መለስ ዜናዊ በየእስርቤቱ የሚያስደበድባቸው የዴሞክራሲ ታጋዮች፣ የሚደርስባቸውን ህመም እሱም እንዲቀምሰው ከተደረገ ሊሰማው ይችላል። ካልቀመሰው እንዴት ሊሰማው ይችላል? 
የስብሰባው ሰአት እየተቃረበ በሄደ መጠን የሙላቱ ቁጣ እየጨመረ ሄደ። መለስ ይቀመጣል ተብሎ የተገመተበትን ቦታ በካርታ ጭምር ሲያጠና ቡጢውን እንደጨበጠ ነበር። እንባው ኮለል ብሎ ሳይወርድም አልቀረም። እንዲህ ያሉ እንባዎች ከቁጭት ኩሬ የሚፈልቁ ናቸው። 
የመጨረሻዋ ሰአት እንደተቃረበች ሙሌ፣
“ይህን ታሪካዊ ድርጊት የምፈፅመው እንደ ልደቱ አያሌው ባንዴራ ለብሼ መሆን አለበት” የሚል አሳብ አቀረበ። ይህ ግን ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ። ስሜታዊ መሆን እንደማይገባ ተነገረው። ተራ ጋዜጠኛ ሆኖ፣ በስልት ወደ መለስ ዜናዊ መጠጋት እንዳለበትም ተመከረ። ለማንኛውም በሚል ሙሌ በተደጋጋሚና በልዩ ልዩ ቅርፅ ፎቶ እንደዲነሳ ተደረገ…. 
የስብሰባው ሰአት ደረሰ። መሪዎች ገቡ። ጋዜጠኞችም ወደ ውስጥ ጎረፉ። ሙሌም እንደማንኛው ተራ ጋዜጠኛ ተቀላቅሎ ወደ ውስጥ ዘለቀ። ከስብሰባው ውጭ ያሉ ጋዜጠኞች ጊዜ ለመቆጠብ ለዜናው የሚሆኑ አንዳንድ ነጥቦችን በቁራጭ ወረቀት ላይ መያዝ ጀማመሩ፣
“….በመለስ ዜናዊ አገዛዝ የተበሳጨ አንድ ጋዜጠኛ የመለስ ዜናዊን ሁለት ከንፈሮች በቡጢ አነደደ!”

“…መለስ ዜናዊ የቡጢን ህመም ቀመሰ! በሆስፒታል እርዳታ እየተደረገለት ሲሆን ለህይወቱ ሳያሰጋው አይቀርም።”“…የአይን ምስክሮች እንደገለፁት የሙላቱ ቀኝ እጅ የመለስ ከንፈሮች ላይ ባረፉባት ደቂቃ፣ ‘ጧ!’ የሚል የፍንዳታ ድምፅ ተሰምቷል።”“…ከሃኪሞች የሾለከ ዜና እንደሚገልፀው የመለስ ከንፈር ከባድ የመተርተር አደጋ ደርሶበታል።”“…የቤልጂየም ሃኪሞች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እርዳታ እያደረጉለት ነው”“…የመለስ ጥርሶች አለመጎዳታቸው ታወቀ! ዝርዝሩን እንደደደረሰን እንገልፃለን…”

እደጅ የነበሩት የእቅዱ አዘጋጆች ውጤቱን ለመስማት በጥፍራቸው ቆመው እየጠበቁ ነበር። ትንፋሽ አጥሯቸው በመጠባበቅ ላይ ሳሉም ሙሌ ካሜራውን እንዳንጠለጠለ ተመልሶ ብቅ አለ፣

“ምነው?” ሲሉ ጠየቁት።በረጅሙ ተነፈሰ።“አጣኸው እንዴ?”“ማየትማ አይቼዋለሁ።”“እና ታዲያ ለምን አልመታኸውም?”“ፎቶ የማነሳው በመምሰል ስጠጋው፣ እሱም ልመታው እንዳሰብኩ ገባው መሰለኝ ፍርሃቱን አይኖቹ ውስጥ አየሁ። ልመታው እችል ነበር። አጠገቡ ነበርኩ…”በከበቡት ሰዎች ዙሪያ ጥልቅ ዝምታ ወደቀ። ቃል የሚተነፍስ ጠፋ። በዚህ ጊዜ ሙሌ እንዲህ ሲል ፀጥታውን ሰበረው፣

“ፎቶግራፍ ግን አንስቼዋለሁ። ካላመናችሁኝ ላሳያችሁ እችላለሁ!”
የቅዳሜ ማስታወሻ ተስፋዬ ገብረአብ 

የአለማየሁ እህት 
          ሳሊምቢኒ ጥቅምት 1 ቀን፣ 1890 በያዘው ማስታወሻ፣ አጤ ምኒልክ ትግራይ በነበሩ ጊዜ የተፈፀመ አንድ ታሪክ አንስቶአል።         

          በዚያን እለት ምሽት አጤ ምኒልክ ትግራይ ላይ ከተከሉት ንጉሳዊ ድንኳናቸው ተቀምጠው የቀጠሯትን አንዲት ሴት እየጠበቁ ነበር። እንደተጠበቀውም ማምሻው ላይ ወይዘሪቷ በሁለት አሽከሮች አጀብ በበቅሎ እየሰገረች ከአጤ ምኒልክ ድንኳን ደረሰች። በአካባቢው ብዙ ግርግር አልነበረም። ጥቁር ካባ የደረበች፣ በአበሻ ቀሚስ የደመቀች፣ ጠይም ረዘም ያለች ወይዘሪት ከበቅሎ እንደወረደች በጥድፊያ ወደ ንጉሱ ድንኳን እንድትዘልቅ ተደረገ። ይህች ሴት አልጣሽ ቴዎድሮስ ትባላለች። የአጤ ቴዎድሮስ ሴት ልጅ ስትሆን፣ የአጤ ምኒልክ ደግሞ የመጀመሪያ ሚስት ነበረች።

ንጉሱ ባዘዙት መሰረት ሁለቱ የቀድሞ ባልና ሚስት በአንድ ገበታ ላይ ለእራት ቀረቡ። የታሪክ መፃህፍት በደፈናው፣ “መሶብ ቀረበ” ብቻ ብሎ ይገልፀዋል። ርግጥ ነው ይህ ቃል በቃል በበርካታ በመፃህፍት ተገልፆአል። ሁለቱ የቀድሞ ባልና ሚስት በዚያን ሌሊት አብረው ማደራቸውም ተፅፎአል። የራት ቆይታቸው ረጅም ነበር። ሆኖም ምኒልክና አልጣሽ ራት እየተመገቡ የተጨዋወቱት አልተመዘገበም። እንግዲህ ደራሲ እንደመሆኔ፣ በዚያን ምሽት የተነጋገሩትን የመስማት ችሎታና መብት አለኝ። ታሪክን በማጣቀስ በመሶቡ ዙሪያ በምናብ ላቆያችሁ፣

አጤ ምኒልክ እንዲህ ሲሉ ጠየቁ፣“ጤንነትሽ እንዴት ነው አልጣሽ?”“እኔማ ምን እሆናለሁ ብለሁ ነው? በእግዚአብሄር ፈቃድ አለሁ። የኛ ነገር እንዲህ መላ ማጣቱ ያንገበግበኛል እንጂ። በተለይ የአለማየሁ ነገር፣ ወንድም እንደሌለው፣ እህት እንደሌለው እንዲህ ሆኖ ሲቀር….”“ጥሩወርቅ ናት ያጠፋች። ይሂድ ብላ ፈቀደች። ‘አባቱ እንዲማርለት ይፈልግ ነበር’ ብላ ለእንግሊዞቹ ነገረቻቸው። ወላጆቹ ተፈቀዱ ምን ይደረጋል? ሁላችንስ በዚያን ግዜ ምን አቅም ነበረን? አምላክ የፈቀደው ሆኖአል…”“አልሆነላትም እንጂ ጥሩወርቅ  ልትለየው መች ፈለገች?”አልጣሽ እንባዋን እያባባሰች ቀጠለች፣ “…የአለማየሁ ነገር ለመሸሻ የእግር እሳት እንደሆነበት አለ። ምንስ ቢሆን ለአንድ ወንድማችን መች እናንስ ነበር? ጊዜ ነው የጣለን። እርስዎስ ቢሆኑ ከኛ ጋር የወንድም ያህል አይደሉም እንዴ? የኔን ይተውት? ምን እንደበደልኩዎት ባለውእም ትተውኝ ሄደዋል። አባቴ ባባትዎ ላይ በፈፀመው ቂም ይዘው ይሆናል…”“ክፉ አትናገሪ አልጣሽ? የማይሆን ሆኖብኝ ትቼሽ መሄዴን አጥተሽው ነው? መቸ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነበርኩ? ወርቂት አሳልፋ ለቴዎድሮስ ሰጥታ ልታስገድለኝ አልነበር? ምኑን ይዤ አንቺን ይዤ ልጓዝ? የችግር ሆኖ እንጂ ካንቺ የበለጠ ተገኝቶ መች ሆኖ?”“ቢፈልጉ እንኳ ከተረጋጉ በሁዋላ ‘አልጣሽ የት ደረሰች?’ ብለው በጠየቁ ነበር። እርስዎ ግን ሌላ አገቡ…”“ይኸው ፈልጌ አገኘሁሽ አይደለም እንዴ? ከልቤ ያልነበርሽ ቢሆን መች እጠራሽ ነበር? ደሞስ ብቻዬን የማደርገው መች ሆኖ? መኳንንቱ አሉ…”“እሱስ ልክ ብለዋል። ሆድ ቢብሰኝ ነው። ‘ንጉሱ ጠርተውሻል’ ብለው ሲሉኝ አልቅሻለሁ። የልጅነት ትዳራችን እንዳልታመመ አወቅሁ። እንዲያው ልጠይቆትና ከመረሃቤቴዋ ባላባት ልጅ ከባፈና ጋር እንዲህ መጣበቅዎ ለምን ይሆን? ምናምን አስነክታዎታለች ነው የሚባል…”አጤ ምኒልክ ምላሽ ሳይሰጡ ዝም አሉ፣

“እንዲህ ተጣብቀው ሲያበቁ ደግሞ ምነው ሳያነግሷት መቅረትዎ?”

“ባፈና ስምንት ልጆች አሏት። ከሷ ጋር መንገስ የማይሆን ነበር” ሲሉ መለሱ።“ቢሆንም መቸም ይወዷት ነበር። መልኳ እንኳ ምንም የማይወጣላት ዘንፋላ ናት አሉ። በእድሜ ግን እናትዎ ትሆናለች ሰማን። ይህን ስሰማ አለቀስኩ። እኔ ምን ቢጎድለኝ ነው? ምን በድያቸው ነው? ብዬ ልቤ ተሰበረ።”አሁንም ምኒልክ ምንም ምላሽ አልሰጡም። “ባፈና ዙፋንዎን ለመጣል ተንኮል ሰርታ ነበር ሰማን…”“ሰዎች አሳስተዋት ነው”“ስለሚወዷት ይሸፋፍኑላታል መቼም። አስነክታዎታለች እንጂ …”እንደገና ምኒልክ ዝምታን መረጡ፣“ወልዳለዎት ነበር መባሉ እውነት ነው?”“ልጁ ባጭሩ ተቀጨ እንጂ ወልዳልኝ ነበር…”“ከጉራጌ ሴት የሚወለድ ኢትዮጵያን ለብዙ ዘመን ይገዛል የሚል ትንቢት ተነግሮ መኳንንቱ ሁሉ ከጉራጌ ሴት ተዋልዷል ይላሉ።” አለች አልጣሽ በጎን አይኗ ንጉሱን እያየች፣ምኒልክ ፈገግ አሉ። አልጣሽ ቀጠለች፣“እርሶም ይህን ትንቢት አምነው  ከቶሮ ልጅ ከወለተስላሴ ወልደዋል ሰማን።”“ልክ ነው። የቶሮ ልጅ ሁለት ወልዳልኛለች…”ከጥቂት ዝምታ በሁዋላ አልጣሽ ወሬ ቀየረች፣“ጣይቱስ እንዴት ናት?”“አጋዤ ናት…”“ልጅ ባለመውለዷ ይሰማት ይሆን?”“ጣይቱ ብርቱ ናት። ስለልጅ ሳነሳባት  14 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ልጃችን ነው ትላለች። አምላክ ልጅ ከለከላት…”“እኔ እወልድሎት አልነበር? ችላ አሉኝ እንጂ”“መች ችላ አልኩ? ይኸው መጣሽ አይደል? እግዚአብሄር ፈቃዱ ከሆነ አንቺ የምትወልጂው ልጅ ይነግስ ይሆናል…”በዚያን ሌሊት አጤ ምኒልክና አልጣሽ አብረው ማደራቸውን ጳውሎስ ኞኞ መፅሃፉ ላይ ተርኮታል። እንደታለመውም ወይዘሪት አልጣሽ ከንጉሱ አረገዘች። ‘ከሁለቱ የታላላቅ ነገስታት ዘር የሚወለደው ልጅ ኢትዮጵያን ለዘልአለሙ ይገዛል’ የሚል ትንቢት ከአዲስአበባ ጆሮ ደረሰ። አጤ ምኒልክም ይህን ተስፋ በማድረግ ከመጀመሪያ ሚስታቸው የሚወለደውን ህጻን በናፍቆት ይጠብቁ ጀመር። ህፃኑ ለመወለድ አንድ  ወር ያህል ሲቀረው ከአልጣሽ ወንድም ከመሸሻ የተላኩ ሁለት መልእክተኞች አዲስ አበባ በመምጣት አጤ ምኒልክን ለብቻ ለማነጋገር ጠየቁ። እንደተፈቀደላቸውም ገብተው አሳዛኝ መርዶ ለንጉሱ ነገሩ።“አልጣሽ አርፋለች” የሚል ነበር።አልጣሽ ከመውለዷ በፊት በእቴጌ ጣይቱ ትእዛዝ በመርዝ መገደሏን ሳሊምቢኒ ፅፎአል።————————————(በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ትረካ። የታሪክ ምንጭ፡ ፃውሎስ ኞኞ፣ ‘አጤ ቴዎድሮስ’ ገፅ 439 – 440) 

የቅዳሜ ማስታወሻ ተስፋዬ ገብረአብ 

የኢህአፓ መድፍ ተሰማ! 
ኢህአፓ ተባሉት ሰዎች የኮሎኔል መንግስቱን መፅሃፍ ስካን አድርገው በድረገፅ ሲለቁት ከተቃወሙት አንዱ እኔ ነበርኩ። የተቃወምኩበት ምክንያት፣ “ለኮሎኔሉ መብት ጥብቅና ለመቆም”፣ ወይም “አሳታሚውን ከኪሳራ ለማዳን” አይደለም። ከመርህ አንፃር ነበር። ባህሉ በጣም አደገኛ መሆኑን በመረዳት ነበር።ድርጊቱ ፀረ እውቀት ስለሆነ ነበር። ተራ የንግድ ጉዳይ አልነበረም። አምርሬ የተቃወምኩት በተለይም በቀጥታ እኔንም ስለሚመለከተኝ ነበር። 

ነፃነት አሳታሚ፣ “የደራሲው ማስታወሻ”ን ባተመ ጊዜ፣ እነዚህ የኢህአፓ ሰዎች ተመሳሳይ ድርጊት ፈፅመው፣ ጉዳዩ ወደ ህግ ማምራት ሲጀምር ከዌብሳይቱ ላይ ተነስቶአል። የነፃነት አሳታሚ ስራአስኪያጅም ጉዳዩን በኢሜይል አሳውቆኝ ነበር። ከዚያ ወዲህ ምናልባት ይህን መሰል ድርጊት አይደገምም ይሆናል ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። በኮሎኔል መንግስቱ ላይ ግን ተደገመ። ይህን ድርጊት የፈፀሙት የኢህአፓ ሰዎች መሆናቸው ስለታወቀ፣ “አሳዛኝ ዜና” በሚል ርእስ ጉዳዩን አውግዤዋለሁ። ያንን ተከትሎም የኢህአፓ ሰዎች በድረገፆቻቸው ላይ ተረትና ምሳሌ በበዛበት እንቅልፋም ፅሁፍ ሲሳደቡ ከረሙ። በግል በፃፉልኝ ደብዳቤም፣
“ቀጣዩ መፅሃፍ ገበያ ላይ በዋለ ማግስት ስካን አድርገን እናሰራጨዋለን” ሲሉ ዛቱብኝ። 

አያደርጉትም አይባልም።ምክንያቱም SAMSUNG ALL IN ONE የተባለ ዘመናዊ መድፍ መታጠቃቸውን አስመስክረዋል። ባዙቃ በተንበለበለበት ጦርነት ላይ ተካፍያለሁ። በዚያን ጊዜ ግን አሁን የፈራሁትን ያህል አልፈራሁም። ኢህአፓ ይኸው 100 ዶላር በተገዛች አንዲት ማሽን ብእረኞችን ፍርሃት ለቆብናል። ጓደኞቼን አማክሬ ነበር፣

“ከኢህአፓ ጋር ፀባችሁ ምንድነው?” ብለው ጠየቁኝ።“እንኳን ፀብ ሊኖረን በህይወት መኖራቸውንም በቅርቡ ነው የሰማሁት” ስል መለስኩ።

እውነቴን ነው። ኢህአፓ የሚባል መኖሩን የሰማሁት እዚህ አውሮፓ ከመጣሁ በሁዋላ ነው። ኬንያ እያለሁ፣ ቶልቻ የሚባል ቆንጆ ዱለት የሚሰራ ባለምግብ ቤት ነበር። ኢህአፓ ነው ሲሉ ሰምቻለሁ። ሌላ ደግሞ፣ ጎሳዬ የሚባል እንደ ቁራ የሚጮህ ሰው ዘፈን ዘፍኖ ካሴቱን ካልገዛችሁን ብሎ አስቸግሮን ሁለት ገዝቼዋለሁ። እሱም፣ “ኢህአፓ ነኝ” ሲለኝ ሲቀልድ ነበር የመሰለኝ። በተረፈ “ኢህአፓ ሞቶ ተቀብሮአል:: አንተ የት ነበርክ እስከዛሬ?” ብለው የጠየቁኝ አሉ። “ተቀብረዋል ወይስ አልተቀበሩም” የሚለው የሚያከራክር ሊሆን ይችላል። ሳስበው ግን፣ “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” ሆነዋል። ስለዚህ አሁን “መፍትሄው ምንድነው?” የሚል ነበር።

“የአበሻ ጀብዱ” ሚለውን መፅሃፍ ሳነብ አንድ በጣም የገረመኝ ነገር ነበር። ሰራዊቱ ከፋሽስት ኢጣልያ ጋር ሊዋጋ ሲጓዝ ከጣልያን ሰራዊት በላይ እያሸመቁ የጎዱት የራያ ሽፍቶች እንደነበሩ ቼኮዝላቫኪያዊው ፅፎአል። አሁን ያሳሰበኝ በረከት ስምኦን ሳይሆን፣ የኢህአፓ መድፈኞች ሆነው ተገኙ። ስጋቴ ተራ ስጋት አይደለም። “የስደተኛው ማስታወሻ”ን ለማተም ስደራደረው የነበረው አሳታሚ፣ ከኮሎኔል መንግስቱ መፅሃፍ ስካን መደረግ በሁዋላ፣ 

“ችግሩን እያየኸው ነው። ምንም ዋስትና የለንም።” ብሎ ቀዘቀዘብኝ።

እንግዲህ ኢህአፓ ድል አድርጎአል። ያሰበው ተሳክቶለታል። ይህ ከነበረ ምኞታቸው “ቺርስ” ቢባባሉ ይገባቸዋል።  

Blogger. 

የቅዳሜ ማስታወሻ ተስፋዬ ገብረአብ 

የቴዲ አፍሮ ፍቅረኛ 
ያቺን የማትረሳ ቆንጆ ልጅ የተዋወቅሁዋት አስመራ ላይ ሲሆን፣ ከካቴድሪያል ወደ ቲራቮሎ በሚጓዘው ታክሲ ላይ ተሳፍሬ ነበር። ልጅቱ ፒኮክ የተባለችውን ወፍ ነበር የምትመስለው። ታክሲው ላይ ከሁዋላ አብረን ነበር የተቀመጥነው። “ላናግራት ወይስ ይቅርብኝ?” እያልኩ ሁለት ልብ ሆኜ እያመነታሁ ቆየሁ። እኔ ደጋግሜ ባያትም፣ እሷ አንድ ጊዜ እንኳ ዘወር ብላ አላየችኝም። ከሞባይል ቴሌፎኗ ጋር ተመስጣ እየተጫወተች ነበር።  
(መቸም እንዲህ ያለ ነገር የገጠመኝ ደብረዘይት ላይ ቢሆን ለኔ ቀላል ነበር፣

“ጭሷ! ሞባይልሽ ጭስ ናት!” ብዬ እጀምር ነበር።

ወይም ደግሞ፣ “ነፍሷ! ሞባይልሽ ነፍስ አላት!” በተባለ።

“አመስግናለሁ” ካለች ደግሞ፣
“አንቺም እንደ ሞባይልሽ ጭስ ነሽ! የልቤን ልንገርሽ? አንቺ ማለት የ2008 ኖኪያ ማለት ነሽ” በሚል አድናቆትና ቀልድ በመንደርደር ወደ ቁምነገሩ መግባት በተቻለ። 
በርግጥ የደብረዘይት የለከፋ መንገድ ይሄ ብቻ ነው ማለት አይቻልም። 

“ስሚ አንቺ ብጣሻም! ባለካሜራውን ሞባይል ብትይዢ ብርቅ መሰለሽ?” ብሎ ማብሰሉን የሚጀምርም ይኖራል። 
አሁን እንኳ ባለካሜራው ብርቅ አይደለም። አንድ ሰሞን ግን ሪፖርተር ጋዜጣ፣ “ባለካሜራው ሞባይል ስልክ ከአንድ ግለሰብ ላይ ተሰረቀ” ብሎ ዘግቧል። እንግዲህ በእነ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር ዘመን፣ “ፍቅረኛዬ ሰአት ያሰረች ናት” ተብሎ እንደሚፎከረው ማለት ነው – አምላክ ነፍሱን በገነት አፀድ ውስጥ ያሳርፋት!…)  
እዚህ አገር ግን እንግዳ እንደመሆኔ ኤርትራውያን ሴቶችን እንዴት ማነጋገር እንደሚገባ አላውቅም ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ ትግርኛ ይቸግረኛል። በዚያን ጊዜ ጥቂት ትግርኛ ስናገር ወደ ተራራ እንደሮጠ ሰው ከላይ እስከ ታች ድካም ይሰማኝ ነበር። አሁን እንኳ አቀላጥፌ ከመናገር ባሻገር፣ መፃፍና፣ ማንበብም ጀምሬያለሁ። 
የሆነው ሆኖ ከዚህች ጠጉሯን እንደ ጉድ ከለቀቀች ፒኮክ ጋር በምን ዘዴ መነጋገር እንዳለብኝ እያሰላሰልኩ ሳለ፣ ሞባይል ስልኳ መጥራት ጀመረ። የስልኳ የጥሪ ድምፅ የቴዲ አፍሮ፣ “ዳህላክ ላይ ልስራ ቤቴን” የሚለው ነበር። 
ፒኮክ ለስልኩ ጥሪ ምላሽ ስትሰጥ ዘፈኑ ተቋረጠ፣

“እየመጣሁ ነው። ሲኒማ ሮማ ደርሻለሁ” ስትል ምላሽ ሰጠች።

አሁን የወሬ ርእስ አገኘሁ፣

“አምቼ ነሽ እንዴ?” ስል በትግርኛ ጠየቅሁዋት።

“አይደለሁም” አለችና የሞቀ ሳቅ ሳቀች።

አቀማመጤን አስተካከልኩና ጨዋታዬን ቀጠልኩ፣

“ስልክሽ ላይ የዘፈነውን ድምፃዊ ታውቂዋለሽ?”

ሳቀች። ስትስቅ እንደጉድ ታምራለች። ወይ መከራ!
በጥያቄዬ የተገረመች መስላ፣

“ቴዲን የማያውቅ ማን አለ?” አለች።

በዚያን ጊዜ ቴዲ እስር ቤት ስለነበር ይህንኑ ጠየቅሁዋት፣

“መታሰሩን ሰምተሻል?”

“እውይ! አዎ ሰምቻለሁ። ምናድርጎ ነው ግን ያሰሩት?”

“ለምን እንዳሰሩት አልሰማሽም?”

“ዕንዲዒ! አሰሩት ሲሉ ብቻ ሰማሁ”

“አማርኛ ትሰሚያለሽ?” ስል ጠየቅሁዋት።

“አልሰማም። ብሰማ ደስ ይለኝ ነበር። የቴዲ ዘፈን ምን እንደሚል እሰማው ነበር…”

“የዘፈኑን ትርጉም አታውቂውም ማለት ነዋ!?”

“አውቀዋለሁ!” አለች በእርግጠኛነት፣ “….የአክስቴ ልጅ አምቼ ናት። ትርጉሙን ነግራኛለች”

“ምን ብላ ነገረችሽ?” 
ፒኮክ በተፈጥሮ ሊፒስቲክ የተቀቡ ከንፈሮቿን ላሰቻቸውና ለወግ ራሷን አመቻቸች። ከማውራቷ በፊት ግን እንደገና በረጅሙ ሳቀች። እና እንዲህ አለች፣ 
“…የቴዲ ፍቅረኛ ኤርትራዊት ነበረች ምሽ? ከዚያ ወያኔ ከአገር አባረራት ምሽ? ሃርማዛት ተባዒሶም ይብል ድማ! ከዚያም ቴዲ ‘ከፍቅረኛዬ ተለይቼ ከምቀር ዳህላክ ላይ ቤት ሰርቼ አብረን እንኖራለን’ ብሎ ዘፈነላት። ቴዲ የፍቅር ሰው ነው አይደለም? ልክ ነኝ ምሽ?” 
“ልክ ነሽ” እንድላት ጓጉታ በሚለማመጡ አይኖቿ እያየችኝ ሳቀች። 
አህ! ታክሲው እኔ ከምወርድበት ቦታ ደርሶ ቆመ። እኔ ወረድኩ። ፒኮክ ወደ ቲራቮሎ መንገዷን ቀጠለች። ከታክሲ ከወረድኩ በሁዋላ፣ እዚያው እወረድኩበት ቦታ ዝም ብዬ ቆምኩ። ታክሲው መንገዱን ሲቀጥል፣ ፒኮክ በታክሲው የጀርባ መስታወት በኩል አንገቷን ጠምዝዛ ስታየኝ አየሁዋት። “ቻዎ!” ለማለት እጄን ብድግ አደረግሁ። ፈገግ ሳትል አልቀረችም….        

የቅዳሜ ማስታወሻ ተስፋዬ ገብረአብ 

የንጉሰ ነገስቱ እናት 

ሳቂታ ውብ ጥርሶችና ታማኝ አይኖች ያሏት ሸዋረጋ የምትባል አንዲት ልጅ ነበረች። ነዋሪነቷ ወሎ ላይ ነበር። ገና የስምንት አመት ህፃን ሳለች ወላጅ እናቷ ስለሞተችባት ለአንዲት አሮጊት በግርድና ለማገልገል ተቀጠረች። ይህች እድለቢስ ልጅ አባቷን አታውቀውም። እንጀራ ጋጋሪ ከነበረች ወላጅ እናቷ የተገኘ ውርስም አልነበራትም። 

አሮጊቷ በበቅሎ ሲጓዙ፣ እየተከተለች ከበቅሎዋ እኩል መስገር ዋና ስራዋ ሆነ። ምሽት ላይ የአሮጊቷን እግር ታጥባለች። ማለዳ ቤት ትጠርጋለች። ገረድ እንደመሆኗ የታዘዘችውን ሁሉ ትሰራለች። በዚያን ዘመን ሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ልማዱ ነበር። ወታደሮች ወሎን እያቋረጡ ያልፋሉ። ወታደሮች ወደ ዘመቻ ሲሄዱና ሲመለሱ ማየት ለሸዋረጋ የእድገት ትዝታዋ ነው። አንዳንድ ጊዜ ስሜቷ እየተነሳሳ፣ የተቀጠረችበትን የግርድና ስራ በመተው ከወታደሮቹ ጋር ወደ ዘመቻ ትሄድ ነበር። 

በዘመኑ አስተሳሰብ ለአቅመ ሄዋን እንደደረሰች ከምስራቅ ኢትዮጵያ ከመጡ ወታደሮች አንዱ ሸዋረጋን ወደዳት። ምንም እንኳ ችግር ያደቀቃት ገረድ ብትሆንም፣ ቁንጅናዋን በማስተዋል፣ ልበሙሉ ፈገግታዋን በማጤን ሚስቱ አደረጋት። እሷም ቢሆን ከግርድና ይልቅ የአንድ ወታደር ሚስት መሆን እንደሚሻል በማመን ሳታመነታ ወደ ትዳር አለም ገባች። ወታደሩም ግዳጁን ፈፅሞ ሲያበቃ ሚስት ይዞ ወደ ሃረርጌ ተመለሰ። እነሆ! ያቺ ተስፋ አልባ የነበረች ምስኪን ልጅ አሁን የተሻለ ህይወት መኖር ጀመረች።

አንድ ቀን ከባልዋ ጋር ሲጨዋወቱ፣

“ሸዋ! ምንድነው ይሄ አንገትሽ ላይ ያለው ድግምት?” ሲል እንደ ዋዛ ይጠይቃታል።

“ምንም” ትላለች።

“አለምክንያትማ አላንጠለጠልሽውም?”

መልስ ሳትሰጥ ዝም ትላለች፣

ባሏ ጠረጠረ። መስተፋቅር ሊሆን ይችላል ብሎ ስለገመተ ወደ ንስሃ አባቱ ሄዶ ሚስቱ አንገት ላይ ስለታሰረው ድግምት ይናዘዛል። ቄሱ ሚስትየውን ለማነጋገር ይፈቅዱና ባልየው በሌለበት እለት ወደቤት በመምጣት ሸዋረጋን ያነጋግሯት ጀመር።

“እንዲያው ይሄ አንገትሽ ላይ ያሰርሽው ምን ይሆን?”

ሸዋረጋ በልቧ የያዘችው ምስጢር ቢሆንባትም፣ ቄስ ጠይቆ መልስ መስጠት ግዴታ ነውና እናቷ ከመሞቷ በፊት የነገረቻትም ምስጢር ተነፈሰች፣

“እናቴ ናት ያሰረችልኝ…”

“ምን ይሁንሽ ብላ አሰረችልሽ ልጄ?”

“የማን ልጅ መሆኔ ተፅፎበታል ብላ ነገረችኝ…”

“ማናት እናትሽ? ወዴት አለች አሁን?”

“እንጀራ ጋጋሪ ነበረች። የሰባት አመት ልጅ ሳለሁ ሞተችብኝ…”

“እስኪ ወዲህ በይው ልጄ?”

ሸዋረጋ አንገቷ ላይ የታሰረውን ክታብ ፈትታ ለቄሱ አቀበለች። ቄሱ እያማተቡና አንዳች የማይሰማ ነገር እያጉተመተሙ የታሰረውን ክታብ በጥንቃቄ ፈቱት። የተጣጠፈውን ወረቀትም በርጋታ ዘረጋጉት። እናም አነበቡት። በማንበብ ላይ ሳሉ በድንጋጤ ብዛት ትንፋሻቸው ሊያመልጥ ምንም አልቀረውም። በተቀመጡበት ተፈንግለው እንዳይወድቁ፣ መከዳውን ደገፍ ብለው አቀርቅረው ቀሩ። ሸዋረጋ ከቄሱ ድንጋጤ ጋር አብራ ስለደነገጠች አባቷ ማን እንደሆነ እንዲነግሯት ተጣድፋ የጠቀች። ቄሱ ግን የተጠየቁትን በመመለስ ፈንታ መልሰው ለልጅቱ ጥያቄ ያቀርቡላት ጀመር፣

“እናትሽ ስላባትሽ ምን ነግራሻለች የኔ ልጅ?”

“ምንም አልነገረችኝም፣ እሷ ስትሞት ትንሽ ነበርኩ…”

“ምን ትዝ የሚልሽ ነገር አለ?”

“ምንም የለም።”

“መቼም ምንም አልነገረችሽም አይባልም። እስኪ አስታውሺ?”

“ምንም አልነገረችኝም አባቴ። ድሃ ነሽና ከሰው ተጠግተሽ እደጊ! ካደግሽ በሁዋላ ግን ይህን በአንገትሽ ላይ በቆዳ ሰፍቼ ያሰርኩልሽን ወረቀት ለምታምኛቸው ሰዎች አሳዪ’ ብላኝ ሞተች…”

“ከእናትሽ ጋር የት ነበራችሁ?”

“ወሎ ነበርን። እስላሞች ቤት…”

“እናትሽ እስላም ናት?”

“ለመኖር ብዬ ነው እስላም ቤት የገባሁት ብላኛለች።”

“እናትሽ ማንነበር ስሟ?”

“ደስላ” 

ሸዋረጋ ልቧ ተሰቅሎ እንደገና ጠየቀች፣

“ወላጅ አባቴ ማነው?”

“አጤ ምኒልክ ናቸው የኔ ልጅ….” 

* * *

እነሆ! ሸዋረጋ እና ባልዋ ከሃረርጌ ወደ አዲስአበባ ጉዞ ጀመሩ።

አንዲት መጠጊያ ያጣች ወላጅ አልባ ሴት ያገባ የመሰለው ወታደር ከንጉሰ ነገስቱ ሴት ልጅ ጋር ጋብቻ መፈፀሙን ማመን ቸግሮታል። ህይወት እድል ናት። እድል እያዋከበ ወስዶ የንጉስ ልጅ ባል አድርጎታል። በዚህ ምክንያትም ከንግዲህ ህይወቱ ይለወጣል። በርግጥም ሹመት እንደሚያገኝ አምኖአል። የልእልት ባል እንደመሆኑ ተራ ሰው ሆኖ ሊቀጥል አይችልም። ቢያንስ ደጃዝማችነት ማግኘት እንደሚገባው ሳያሰላስል አልቀረም። የንስሃ አባቱ የመከሩትና የነገሩትም ይህንኑ ነው፣

“እድለኛ ነህ። ከንግዲህ ኑሮህ ይለወጣል። ሚስትህን ወደ ንጉሱ ውሰዳት። የእሳቸው ልጅ ነች…”

ባላገሩ ወታደር ይህንኑ ጣፋጭ ህልም እያኘከ፣ ሸዋረጋ ምኒልክን ይዞ ከመናገሻዋ ከተማ አዲስአበባ ገባ። 
* * *
እቴጌ ጣይቱ በጥሞና ካዳመጡ በሁዋላ፣

“አስገቧቸው” ሲሉ አሽከራቸውን አዘዙ።

የተጎሳቀሉ ባልና ሚስት ባላገሮች ከንግስቲቱ እልፍኝ ገብተው ለጥ ብለው እጅ ነሱ። እቴጌ ጣይቱ ልጅቱን አተኩረው መረመሯት። የእናቷን ቁንጅና ይዛ መወለዷን ሳያስተውሉ አልቀሩም። ፈገግ ስትል ፀሃይ ብልጭ ያለ ይመስላል። አይኖቿ የአባቷን እንደሚመስሉም ታዝበዋል። እናቷ ከቤተመንግስቱ ስትባረር ይህች ልጅ የ7 ወር ፅንስ እንደነበረች ያስታውሳሉ። የተፈፀመውን ዝርዝር ነገር ሁሉ ያስታውሳሉ። አሁን ግን ፀፀት ቢጤ ልባቸውን ጫር ሳያደርገው አልቀረም።  

በርግጥ በዚያን ዘመን፣ ቅናት በልምጩ ሸንቁጧቸው የነበረ ቢሆንም በጊዜ ብዛት አሁን ያ ስሜት ጠፍቶአል። ደስላ ከወሎ የመጣች ኦሮሞ ነበረች። አንገቷ እንደ ኪሊዮፓትራ ነበር። ደርበብ ሞላ ያለች በጣም ቆንጆ። አንድ ቀን ከአጤ ምኒልክ ገረዶች አንዷ እመኝታ ክፍላ ድረስ በመምጣት እንዲህ አለቻት፣ 

“የይሁዳው አንበሳ ፈልገውሻል”

“ምነው በዚህ ሰአት?”

ደስላ ገረዲቱን ተከትላ በጨለማ ውስጥ ወደ ንጉሱ የመኝታ ክፍል በመጓዝ ላይ ሳለች፣

“ንጉሱ ለምን ፈለጉኝ?” ብላ ጠይቃ ነበር።

“ወደውሻል! እድለኛ ነሽ” የሚል ምላሽ አገኘች።

ንጉሰ ነገስቱ ከዚያን ቀን ጀምሮ ከዚህች ውብ የወሎ ኮረዳ ጋር የፍቅር ግንኙነት ነበራቸው። በመካከሉ ደስላ ፀነሰች። ማርገዟም ይታወቅ ጀመር። ሆኖም ፍርሃት ይዟት ለንጉሱ ሳትናገር ቀረች። በቤተመንግስቱ ዙሪያ የደስላ ማርገዝ በሹክሹክታ ይወራ ጀመር። ከአጤ ምኒልክ ልጅ መውለድ የሚመኙ ሁሉ፣ ደስላ ከንጉሱ በማርገዟ በቅናት ጦፈዋል። እቴጌ ጣይቱ በወቅቱ ይህን ሁሉ ዝርዝር ቢያውቁም፣ አንዳች ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር አልነበራቸውም። ደስላ ማርገዟን ለንጉሱ ከመንገሯ በፊትም አጤ ምኒልክ ወደ ሰሜን ዘመቱ። ከዘመቻ ሲመለሱ ደስላ ቤመንግስት ውስጥ አልነበረችም። 

… ርግጥ ነው፣ ደስላ ከቤተመንግስት ከተባረረች በሁዋላ አጤ ምኒልክን ፍለጋ ወደ ሰሜን ተጉዛ ነበር። በጉዞዋ ላይ ግን ወለደች። ህፃኗ የንጉሱ መሆኗን መናገር አደጋ ይኖረዋል ብላ ሰጋች። የጣይቱ ሰዎች ይህን ከሰሙ ከነልጇ እንዳያስገድሏት መፍራቷ አልቀረም። ስለሆነም፣ ለራሷም ሆነ ለልጇ ህይወት ስትል ንጉሱን በአካል እስክታገኝ ምስጢሯን በሆዷ መያዝ  መረጠች። የምትጠጋበት ወገን ስላልነበራትም እንጀራ ጋጋሪ ሆና ማገልገል እጣ ክፍሏ ለመሆን በቃ። እንዳለመችው ግን አልሆነም። ታመመችና ህይወቷ አለፈ። 

እቴጌ ጣይቱ ለአሽከራቸው ትእዛዝ ሰጡ፣

“ሰውነቷን ታጥባ ንፁህ ልብስ እንድትለብስ አድርጉ።” 

ደጃዝማችንትን እያለመ ረጅም መንገድ የተጓዘው ወታደር ታሪክ ግን ከዚያ በሁዋላ ከምድረገፅ ጠፋ። ‘እኩያህን ፈልገህ አግባ’ ከሚል ምክር ጋር ለኑሮ የሚሆን ድጎማ ተሰጥቶት ተሰናብቶ ሊሆን ይችላል። 

በዚያው ሰሞን አጤ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ እንደተለመደው እያወጉ ሳለ፣

“ያቺ ይወዷት የነበረች ገረድ ትዝ ትሎታለች?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

“የትኛዋ?”

“ወደ ሰሜን በዘመቱ ጊዜ እዚህ ትተዋት የሄዱት። ከዘመቻ ሲመለሱ እንኳ ‘የት ሄደች?’ ብለው ጠይቀው ነበር። ልናገኛት ስላልቻልን ግን ልናመጣልዎ አልቻልንም”

“አስታውሳለሁ። የወሎዋ ልጅ አይደለችም? ተገኘች እንዴ?”

“የርስዎን ሴት ልጅ በወለደች በሰባት አመቷ ሞታለች።” 

አጤ ምኒልክ ክፉኛ አዘኑ። ልባቸው ሳይሰበር አልቀረም። መረር ባለ አነጋገርም ለእቴጌ ጣይቱ ትእዛዝ ሰጡ፣

“ያለፈው አልፎአል። ስለ እግዚአብሄር ብለሽ ልጄን ፈልጊልኝ?”

“ንጉሰ ነገስት ሆይ! ደስ ይበልዎ! ልጅዎ ተገኝታለች” 

እቴጌ ጣይቱ እልፍኙን ለቀው ወጡ። ሲመለሱም ስምንት ተመሳሳይ ልብስ የለበሱ፣ በተመሳሳይ እድሜ ላይ የሚገኙ ኮረዶችን አስከትለው ገቡ። አጤ ምኒልክ ድራማው ገባቸው። ከስምንቱ መካከል አንዷ ከዚያች በጣም ከሚያፈቅሯት የወሎ ኦሮሞ ወለዷት ልጃቸው ናት ማለት ነው። አጤ ምኒልክ ከዙፋናቸው ተነስተው እንደ እግር ኳስ ተጫዋቾች ቡድን በተርታ የተደረደሩትን ኮረዶች አንድ ባንድ ያስተውላቸው ጀመር። እየተጠጉ መረመሯቸው። እናም ጥቂት እንኳ ሳያመነቱ፣ ሸዋረጋ ምኒልክን ከሴቶቹ መሃል ለይተው እጇን ያዟት፣ 

“ልጄ ይህቺ ናት!” ሲሉም ጮኸው ተናገሩ። አያይዘውም ጨመሩበት፣ “…ጥርሶቿና ፈገግታዋ ቁርጥ የእናቷ ነው!…” 

  (ሸዋረጋ ምኒልክ ለወሎው ራስ ሚካኤል ተድራ ጥር 25፣ (1888?) ወረሂመኑ ተንታ ውስጥ ልጅ እያሱ ሚካኤልን ወለደች። አጤ ምኒልክም ለሚያፈቅሯት ሴት የልጅ ልጅ የንጉሰነገስትነት ስልጣናቸውን አውርሰው አረፉ…)*    (የትረካ ምንጭ ጳውሎስ ኞኞ፣ የካቶሊክ ቄስ  አባ ጃሮሳቭ እንዲሁም የቤተመንግስቱ ቃለጉባኤ ያዥ ወልደማርያም። የተጠቀሱ ቀናቶች ላይ ጳውሎስ ኞኞ አንዳንድ ስህተቶች ስለፈፀመ ዘልያቸዋለሁ።)        

የቅዳሜ ማስታወሻ ተስፋዬ ገብረአብ 

ስብሃት ገብረእግዚአብሄር 
ቅዳሜ ዞሮ ሲመጣ አንዳንድ ጊዜ ከስብሃት ጋር ደብረዘይት እንሄድ ነበር። አንድ ጊዜ እንዲሁ ባቦጋያ ሃይቅ ዳርቻ ከአንድ ወዳጃችን ግቢ ውስጥ እንደ ስጋጃ ከሚለሰልሰው የሳር መስክ ላይ ጋደም ብለን የሃይቁን የማእበል ድምፅ እያዳመጥን ዋልን። ሴት ልጁ ዜና አብራን ነበረች፣

“ለምንድነው ልጅህን ዜና ያልካት ጋሽ ስብሃት?”
“ለምን ነበር መሰለህ? አንዲት በጣም ቆንጆ፣ ስታወራ የምትጥም፣ የምወዳት ዜና የምትባል ሴት ነበረች። እሷን ለማስታወስ በሚል ልጄን ዜና አልኳት…”

ሌላ ቀን ደግሞ አንድ ግሮሰሪ ውስጥ ቁጭ ብለን እየቀማመስን ሳለ በወቅቱ ምስጢር የነበረ አንድ ወሬ ነገርኩት፣

“ህወሃት ችግር ውስጥ እየገባ ነው…”

“ምን ሆኑ?”

“ለሁለት ተከፍለዋል። በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ ሊሆን ይችላል”
ስብሃት ብዙ ጊዜ ወዲያውኑ መልስ ይሰጣል። በዚህ ቀን ግን በፀጥታ ጥቂት አሰበና እንዲህ አለኝ፣
“ቢከፋፈሉ መጥፎ አይደለም። አንዱ ሌላውን ለመብለጥ ሲል በመካከሉ ጥሩ አሳብ ሊያመጡ ይችላሉ። አብዮተኞች መከፋፈል ማይቀር እጣቸው ነው። በቻይናና በኩባ ታይቶአል። ካስትሮና ቼ ይለያያሉ ተብሎ የሚታሰብ አልነበረም..”
በዚያን እለት ከደብረዘይት እንደተመለስን ጎተራ አካባቢ መኪና ውስጥ ቁጭ ብለን ብዙ አመሸን። ስብሃት ደረቅ አረቄ ስለሚጠጣ ፈጥኖ ሞቅ ይለዋል። እና ያን ቀን በመካከሉ ብቻውን መሳቅ ጀመረ። ልክ እንደተኮረኮረ ሰው ነበር የሚስቀው። ከመሳቁ ብዛት እንባው ከአይኑ ወረደ። እንዲህ የሚስቀው አንድ ቀልድ ብልጭ ሲልለት ነው።
“ምንድነው እንዲህ ያሳቀህ?”

“የኦብሎሞቭ አገልጋይ ትዝ ብሎኝ ነው” አለ።

በዚያን ጊዜ ኢቫን ጋንቻሮቭ የተባለው የወርቃማው ዘመን ደራሲ ‘ኦብሎሞቭ’ በሚል ርእስ የፃፈውን መፅሃፍ አላነበብኩም ነበር። ስብሃት ምን ትዝ እንዳለው እንዲህ ሲል አጫወተኝ፣
“…ሽማግሌው የኦብሎሞቭ አገልጋይ በጣም ሰነፍ ነበር። ኦብሎሞብ ከስራ ሲመለስ ቤቱ አልተፀዳም፣ አልጋውም አልተነጠፈም፣

‘ለምንድነው አልጋውን ያላነጠፍከው?’ ይለዋል።

‘ጌታ ኢሊያ ኢሊይች… ባነጥፈውም እኮ መልሶ መበላሸቱ አይቀርም። ብጠርገውም ቤቱ መልሶ ይቆሽሻል..’…”

እንደገና ሲስቅ ከቆየ በሁዋላ እንዲህ አለ፣

“ይኸው እየጠጣን ነው። ከዚያም እንሸናለን። እንደገና ደግሞ እንጠጣለን። መልሰን ደግሞ እንሸናለን። እየጠጣን እየሸናን … እየጠጣና እየሸናን እስከመቼ? …”
አንድ ጊዜ አብረን አመሸንና ሰይጣን ቤት ከሚገኘው ቤቱ አደረስኩት። ከመኪናው ሲወርድ ግን ሚዛኑን መጠበቅ አልቻለም። እርጅናው ተጫጭኖት እንጂ ብዙም አልጠጣም። መኪናዬን ዳር አቆምኩና ላግዘው ወረድኩ። መፅሃፍ መያዣውን የላስቲክ ከረጢት ያዝኩለት። መስሪያቤቱ ለመፅሃፍ መያዣ ሁለት ጊዜ ቦርሳ ገዝቶ ሰጥቶት ነበር። እየጠፋበት ላስቲክ እየያዘ ሲመጣ፣ እኛም ተውነው። ወደ ስብሃት መኖሪያ ቤት የሚያስገባው መንገድ ቀጭንና ኮሮኮንቻማ ነበር። ቤቱ ከመድረሱ በፊት ቆመና፣
 “አንዴ ጠብቀኝ ልሽና” አለኝ።
ወደ አጥሩ ተጠግቶ መሽናት ጀመረ። በመካከሉ በደንገዝጋዛው ጨለማ ውስጥ አንድ ሰው ሲመጣ አየሁ። ጨላልሞ ስለነበር ሰው መምጣቱና ኮቴው እንጂ መልኩ በትክክል አይለይም። ሰውዬው ልክ አጠገባችን ሲደርስ ስብሃት፣ “ኸህህህ!” ሚል የፉከራ አይነት ድምፅ አሰማ። መንገደኛው አላየንም ነበር መሰለኝ፣ ወደ እኔና ወደ ስብሃት ገልመጥመጥ ካለ በሁዋላ ርምጃውን ጨምሮ መንገዱን ቀጠለ። ስብሃት ሱሬውን እየዘጋ፣
“ሰውየው ሲያልፍ ለምን ድምፅ እንዳሰማሁ ታውቃለህ?” ሲል ጠየቀኝ።

“ለምንድነው?”

“የኛ ሰፈር መሆኑ እንዲታወቅ ብዬ ነው”
በርግጥ በስነፅሁፍ እና በታሪክ ዙሪያ ከስብሃት ጋር ማውራት በፍፁም አይጠገብም። በተለይም ኮሚክ እና እንግዳ ጠባይ ያላቸውን ገፀባህርያት አይረሳቸውም። ስብሃት በራሱ ሙሉ ቤተመፃህፍት ነው። በቀላሉ የመኖር ችሎታው በጣም ይመስጠኝ ነበር። ማንንም ለመምሰል የማይሞክር፣ እራሱን የሆነ እና የልቡን ሁሉ እንዳፈቀደው የሚናገር ሰው በመሆኑ እቀናበት ነበር። ህይወትን በመሰለው መንገድ ኖሮባታል። እናም በዚያችው በአደገባት ሰፈር ውስጥ ሩጫውን ወደ መፈፀሙ ተቃርቦአል። አምላክ ጤና እና ተጨማሪ እድሜ ይስጠው… 

የቅዳሜ ማስታወሻ ተስፋዬ ገብረአብ 

የዘነበ ልጅነት 

ዘነበ ወላ “ልጅነት” በሚል ርእስ የፃፈውን ልቦለድ ድርሰት አነበብኩት። በውነቱ የቀድሞ ወዳጄ ዘነበ በጣም አሪፍ መፅሃፍ ፅፎአል። በልቦለድ መልክ ያቅርበው እንጂ የራሱን ታሪክ የፃፈ ነው የሚመስል። ሸማኔው ዜራሞ አባቱ ወላ ሳይሆኑ አይቀሩም። መፅሃፉ ትረካውን ሲጀምር፣ ዘነበ አባቱን ተከትሎ ወደ እቁብ እየሄደ ነበር። ዜራሞ ሬድዮ አለቻቸው። በሰፈሩ ውስጥ ብዙ ሰው ሬድዮ የለውም።  ዜራሞ ሬድዮ ከፍተው ሲጓዙ፣ ጎረቤት ያከብራቸዋል። ከእቁብ ቤቱ ገብተው ቁጭ ከማለታቸው፣ ዜና መነበብ ተጀመረ። የሚያነበው አሳምነው ገብረወልድ ነበር፣

“ዜና እናሰማለን፣ እንደምን ዋላችሁ?” ሲል፣

ከእቁብተኞቹ አንዳንዶቹ፣

“ዛሄር ይመስገን” በማለት ሬድዮኑን እጅ ነሱት።

“ግርማዊ ንጉሰ ነገስት በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ የፓኪስታን ዜጎች ሰባት ሺህ ፓውንድ ርዳታ ላኩ…”

ዜናው ካለቀ በሁዋላ እቁብተኞቹ በዜናው ላይ ውይይት ጀመሩ፣

ሸማኔው ዜራሞ ጥያቄ ጠየቁ፣“ሰባት ሺህ ባውንድ አስር አስር ብሩ አንድ ሁለት ተብሎ ሳባት ሺህ ባውንድ ሞልቶ ነው የተላከው?”“ቢሆንስ ምን ችግር አለው? አገራችን ማሩን ወተቱን ታፈልቃለች። ከዚያ ላይ ቆንጥሮ መላክ ነው” አሉ የእቁቡ ዳኛ።“አቶ ዜራሞ ፓውንድ እንጂ ባውንድ እኮ አይደለም”ሌላው ጣልቃ ገብተው ሌላ ርእስ አነሱ…“…እህል ስንል አንድ ነገር ትዝ አለኝ። በቀደም በቾ ነበርኩ። እህል ጥንቡን ጥሎአል።”ሌላው ደግሞ ሌላ ርእስ አነሳ፣“ይሄ ሬድዮ ግን እንዴት ነው የሚሰራው?”“አባ ጠቅል ምን ይሳነዋል? ትልቁን ጋንጩር አቡነ ጴጥሮስ ሃውልታ ጋ አስሮ ውሎውን ያስለፈልፈዋል”ዘነበ ወላ ጥሩ መፅሃፍ ፅፎአል። ሳይሰለቸኝ ጨረስኩት። የማንኛውንም የድሃ ልጅ ህይወት ያስታውሳል። እንባ እና ሳቅ ሞልተውታል። ልጅነት ውብ ነው። ወደ ጣፋጩ የልጅነት ዘመን  ይዞ ጭልጥ ይላል። 

Advertisements
%d bloggers like this:
search previous next tag category expand menu location phone mail time cart zoom edit close